Fana: At a Speed of Life!

29 ነጥብ 5 ሚሊየን የዶሮ ጫጩቶች ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ ተደርገዋል ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አምስት ወራት 29 ነጥብ 5 ሚሊየን የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶች ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ መደረጋቸውን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ወደ ትግበራ ከገባ ከአንድ ዓመት ጊዜ በላይ ካስቆጠረው የሌማት ትሩፋት ሕዝቡ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል ብለዋል።

ይህ ዕቅድ ለታለመለት ግብ እንዲደርስም ሚኒስቴሩ አስፈላጊ የሚባሉ የዶሮ፣ የእንስሳት፣ የንብ ቀፎና ሌሎችንም ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በዚህም ባለፉት አምስት ወራት 28 ሚሊየን የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶች ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ 29 ነጥብ 5 ሚሊየን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እንዲሁም በርካታ መጠን ያለው የማር ምርት ተመርቶ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲደረግም ሚኒስቴሩ ባለፉት አምስት ወራት 315 ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ተደራሽ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ለሁሉም ክልሎች የግብርና ሽግግር ፍኖተ-ካርታ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ክልሎች ያላቸውን ፀጋ ተጠቅመው የግብርና ሥራዎችን እንዲሰሩ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።

በዚህም እስከ አሁን የጋምቤላ፣ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ፍኖተ-ካርታ መሠራቱን ጠቁመው፥ የሌሎች ክልሎችም በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.