በቻይና በኮሮና ቫይረስ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ48 ነጥብ 2 በመቶ ቀንሷል – የሃገሪቱ ጤና ኮሚሽን
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና በየዕለቱ በኮሮና ቫይረስ አዲስ የሚያዙ ሰወች ቁጥር በ48 ነጥብ 2 በመቶ መቀነሱን የሃገሪቱ ጤና ኮሚሽን አስታወቀ።
ከፈረንጆቹ የካቲት 4 እስከ 11 ባሉት ቀናት በሃገሪቱ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰወች ቁጥር መቀነሱን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
ማክሰኞ 2 ሺህ 15 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙ ሲሆን፥ ይህም ከስምንት ቀን በፊት ከነበረው አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በ1 ሺህ 872 ቀንሷል ነው የተባለው።
ከዚህ ባለፈም ቻይና ግዛቴ በምትላቸው ሃገራትና ራስ ገዝ አካባቢዎች በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በ37 ነጥብ 3 መቀነሱንም ኮሚሽኑ ገልጿል።
በተጨማሪም ከሆስፒታል አገግመው የሚወጡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷልም ነው ያለው ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ።
በዚህም አሁን ላይ ከቫይረሱ የማገገም እድል ከሁለት ሳምንት በፊት ከነበረበት 1 ነጥብ 3 በመቶ አሁን ላይ ወደ 10 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏልም ነው ያለው።
እስከ ማክሰኞ ድረስም 4 ሺህ 740 ሰዎች ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸውን የኮሚሽኑን መረጃ ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች ያመላክታሉ።
ኮሚሽኑ ሁኔታው አሳሳቢ ቢሆንም ውጤታማ እርምጃዎች ከተወሰዱ በኋላ አበረታች ለውጦች ተመዝግበዋል ብሏል።
ምንጭ፦ ሲ ጂ ቲ ኤን
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision