Fana: At a Speed of Life!

በመኪና አደጋ የዓይን ብርሃኑ የተመለሰለት ፖላንዳዊ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለአካል ጉዳት አልያም ለህልፈት ምክንያት የሆነው የመኪና አደጋ የግለሰቡን የአይን ብርሃን መልሷል ይላል ከወደ ፖላንድ የተሰማው ዘገባ።

ግለሰቡ ለሃያ ዓመታት በቀኝ አይኑ ከሚያገኛት ትንሽ የብርሃን ጭላንጭል ውጭ የአይን ብርሃኑን ሙሉ በሙሉ አጥቶ ቆይቷል።

በዚህ ህይዎት ውስጥ እያለ በአንድ ቀን በተፈጠረ ክስተት የህክምና ባለሙያዎች ተዓምር ያሉት አጋጣሚ ተከስቷል።

ያኑስ ጎራጅ የተሰኘው ግለሰብ በአንዱ ቀን መንገድ በማቋረጥ ላይ ሳለ በመኪና ተገጭቶ የዳሌ ጉዳት ያጋጥመውና ሆስፒታል ይገባል።

በሆስፒታሉም ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ህክምናውን እየተከታተለ ሁለት ሳምንታትን ያሳልፋል።

ሆስፒታል በቆየባቸው የመጨረሻዎቹ ቀናት በአንዱ ቀን አይኑን ሲገልጥ ሰዎችንም ሆነ በዙሪያው ያሉ ነገሮችን መመልከት ይችላል።

ጉዳዩ እንግዳ የሆነበት ግለሰብ ሁኔታውን ለህክምና ባለሙያዎች አሳውቆ፥ ሃኪሞቹ በትክክል ማየትና መመልከት መቻሉን ያረጋግጣሉ።

ግለሰቡ ህክምናውን ከጨረሰ በኋላ የአይን ብርሃኑ ሙሉ በሙሉ ተመልሶለት ህክምናውን በተከታተለበት ሆስፒታል የጥበቃ ስራ መጀመሩም ተገልጿል።

የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው የግለሰቡ የአይን ብርሃን መመለስ ከአደጋው ጋር ግንኙነት እንደሌለው ገልጸዋል።

ምናልባትም ህክምናውን ሲከታተል በነበረበት ወቅት የወሰደው የደም መርጋትን ለመከላከል የሚያግዘው መድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች መድሃኒቶች የአይን ብርሃኑ እንዲመለስለት ሳያደርጉ እንዳልቀረም ነው የገለጹት።

ከክስተቱ ጋር ተያይዞ የህክምና ባለሙያዎቹ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርምር ለማካሄድ ያደረጉት ጥረት ግን በግለሰቡ እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀርቷል።

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.