ዳያስፖራው የሀገሩን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ) የዳያስፖራው ማህበረሰብ የሀገሩን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ”ዳያስፖራው ለሀገር ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ዳያስፖራው ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለማገዝ አቅሙም እውቀቱም እንዳለው አውስተዋል።
በመሆኑም ከዚህ ቀደም የነበረውን አስተዋጽኦ በማጠናከር በተለይ ደግሞ ለሰላም የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
”በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የሚኖርበት ማህበረሰብ የዴሞክራሲ ባህሉ ያደገ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ይህ ልምድና ተሞክሮ ለኢትዮጵያም ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በሃሳብ የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት እንዲኖርና የሃሳብ ክርክር በስፋት እንዲለመድም ዳያስፖራው የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አብረሃም ስዩም በበኩላቸው፥በአሁኑ ወቅት ዳያስፖራው ከሀገሩ ሰላም በላይ የሚያሳስበው ጉዳይ የለም ብለዋል።
በተለያዩ የኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራትና ባለሃብቶችን ለመሳብ የሀገር ሰላም ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።
የሀገርን ሰላም እውን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ “ሁሉም ለሰላም ዘብ ሲቆም” መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበርም “ስለ ሰላም የሚሰራ ኮሚቴ” በማቋቋም ለሀገር ሰላምና የህዝቦች ደህንነት ይሰራል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሌኒ ገብረመድህን እንደገለጹት፥ ስለ ሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ ሲታሰብ “እኔ ምን ማበርከት እችላለው?” የሚለውን ይዞ መነሳት ያስፈልጋል።
በመሆኑም አንድ በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም መስክ ሀገሩን ሊያግዝ ይገባል ነው ያሉት።
የዳያስፖራው ማህበረሰብ ሁል ጊዜ የተመቻቸ ነገርን መጠበቅ ሳይኖርበት በእኔነት ስሜት ለኢትዮጵያ ስኬት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
በውይይቱ ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል አስተያየታቸውን የሰጡ የዳያስፖራ አባላት ለሀገራቸው ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ለዜጎቿ ምቹና ፍፁም ሰላም የሰፈነባት ለማድረግ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
በተለያዩ የውጭ ሀገራት ኑሯቸውን ያደረጉ ከ3 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በውጭ ሀገራት እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።