ለአፍሪካ አህጉር አቀፍ መረጃና ደህንነት ውጤታማ አገልግሎት ኢትዮጵያ ድጋፍ ታደርጋለች- ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለአፍሪካ አህጉር አቀፍ መረጃ እና ደህንነት ውጤታማ አገልግሎት ኢትዮጵያ የጀመረችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።
የአፍሪካ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኮሚቴ ዋና ፅህፈት ቤት ህንፃው በአዲስ አበባ እየተካሄደ ካለው ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን ነው በዛሬው እለት በይፋ መመረቁን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በህንፃው ምርቃት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፥
ለአፍሪካ አህጉር አቀፍ መረጃ እና ደህንነት ውጤታማ አገልግሎት ኢትዮጵያ የጀመረችውን ድጋፍ ታጠናክራለች ብለዋል።
የአፍሪካ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ኮሚቴ ዋና ፅህፈት ቤት ዘመናዊ ህንፃ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ላይ መገንባቱ፤ ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ሰላም እና ፀጥታ የምትጫወተው ትርጉም አዘል ሚና መገለጫ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአፍሪካ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ኮሚቴ ዋና ፅህፈት ቤት ዘመናዊ ህንፃ መገንቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቁልፍ ቦታ የኢትዮጵያ መንግሥት መስጠቱን አስታውሰዋል።
የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ን’ጉዌማ ‘ባሶጎ ለህንፃ ግንባታ ሙሉ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጋቸውን በማስታወስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አመስግነዋል።
በመጨረሻም ለአገልግሎት የበቃው ዘመናዊ ህንፃ ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ጠንካራ አመራር ለሰጡት የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አድንቀዋል።