Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው መሰረታዊ የምግብ ምርቶችን ወደ ሃገር ውስጥ እንዲያስገባ የሚፈቅድ የአሰራር መስፈርት ወጣ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሰረታዊ የምግብ ምርቶችን ወደ ሃገር ውስጥ እንዲያስገቡ የሚፈቅድ አዲስ የአሰራር መስፈርት አወጣ።

መስፈርቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለ የንግድ ድርጅታቸው የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ስንዴና ሌሎች የምግብ ምርቶችን የራሱን የውጭ ምንዛሪ በመጠቀም እንዲያስገቡ የሚያስችል ነው።

በስራው መሰማራት የሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ባለፉት ሁለት አመታት በውጭ ሃገር በሚገኝ አካውንታቸው ሲንቀሳቀስ የነበረ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወይም ተመጣጣኝ መጠን ያለው ዩሮ ወይም የእንግሊዝ ፓውንድ መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አካውንቱ ካለበት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

በዚህ መሰረትም ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች የሚያሟላና በሃገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ በዳያስፖራ አባላት በጋራ የተቋቋመ ኩባንያን በመጠቀም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፈቃድ ማውጣት ይችላሉ።

አዲሱ መስፈርት ዳያስፖራው የምርት አቅርቦትን መጨመር በሚያስችልና ከዚህ በፊት ክልከላ ተጥሎበት በነበረ ዘርፍ ላይ እንዲሰማራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የገበያ መረጋጋትን እንደሚያመጣ ታምኖበታል።

ከዚህ ቀደም በዚህ የንግድ ስራ ላይ መሳተፍ የሚችሉት መንግስታዊና ውስን የሃገር ውስጥ አስመጪዎች እንደነበሩ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.