አሸባሪው ህወሓት ተስፋ በመቁረጡ ምክንያት ያገኘውን ሁሉ በኢሰብዓዊነት እየጨፈጨፈ ነው -አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “አሸባሪው ህወሓት ተስፋ በመቁረጡ ምክንያት ያገኘውን ሁሉ በኢሰብዓዊነት እየጨፈጨፈ ነው” ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች ውስጥ ንጹሐንን መግደሉን፣ ማፈናቀሉና ሀብት ንብረት መዝረፉንና ማውደሙን አስታውሰዋል።
“ቡድኑ ከመንግስት ንብረት በላይ የግለሰቦችን ሀብትና ንብረት እየዘረፈ ያለ ግፈኛ የሽብር ቡድን ነው” ሲሉ የአረመኔነቱን ጥግ ገልጸዋል።
ሊታገዙ እንጂ ሊዘረፉ የማይገባቸውን አቅመደካማ አረጋዊያንን እና ማየት የተሳናቸው አካል ጉዳተኞችን ሁሉ ሳይቀር እየዘረፈ ያለ ከሰብዓዊነት የራቀ መሆኑንም አስረድተዋል።
ቡድኑ ከቀድሞው በከፋ መልኩ ከሰብዓዊነት ርቆ የአረመኔነትና የአውሬነት ባህሪ ተላብሶ ያገኘውን ሁሉ በኢሰብዓዊነት እየጨፈጨፈ ያለው ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለገባ እንደሆነ አመልክተዋል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሸባሪው ህወሓት አውሬ መሆኑን ተረድቶና ተገንዝቦ ቡድኑን ለመደምሰስ በሚደረገው እንቅሰቃሴ ግንባር ቀደም ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ቡድኑ ኢትዮጵያን ባስተዳደረበት ወቅት በዙ በደሎችን ማድረሱን ጠቅሰው፤ ዘረፋና ዜጎችን በማስመረር ለስደት መዳረግ ተግባሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
ዘራፊው ቡድን የጊዜ ጉዳይ እንጂ አሁን እየፈፀመ ያለው አረመኔያዊ ድርጊት በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የሚመከት መሆኑን ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
‘ታላቋን ትግራይን ለመመስረት ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት’ ብሎ ለተነሳው አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እንዲጥል የአፋር ህዝብ እንደማይፈቅድለት ገልጸዋል።
ቡድኑ በአፋር ህዝብ የተባበረ ክንድ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሚገኝም አቶ አወል አርባ ገልጸዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!