ዋልያወቹ ከጋና የሚያደርጉት የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በኦርላዶ ስታዲየም ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) እና የጋና የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም እንዲካሄድ ኢትዮጵያ መምረጧን የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ገለፀ::
የባሕር ዳር ስታዲየም በካፍ ከታገደ በኋላ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሀገር ውጭ ለማድረግ ተገዷል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአማራጭነት ኬንያ፣ ዚምቧቤን እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራትን መርጧል።
ሶስቱም ሀገራት ይህንን ጨዋታ ለማስተናገድ ፈቃደኝነታቸውን ገልፀዋል::
ነገር ግን የዚምቧቤ ስታዲየም የዚምቧቤን እና የኢትዮጵያን ጨዋታ ብቻ እንዲያስተናግድ በገደብ የተፈቀደለት እንጂ ሌላ ጨዋታ ማካሄድ እንደማይችል ካፍ አረጋግጧል::
ጨዋታውን ለማስተናገድ ኬንያ ፈቃደኝነቷን የገለጸች ቢሆንም÷ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ዚምቧቤ ለመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ማቅናቱ ስለማይቀር፤ በአንድ የአውሮፕላን ጉዞ እና መጠነኛ ወጪ ጨዋታውን በደቡብ አፍሪካ ለማድረግ ወስኗል።
በመሆኑም ጨዋታው ፊፋ በሚያስቀምጠው ቀን በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም እንዲካሄድ ፌዴሬሽኑ ከደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ተስማምቷል መባሉን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!