Fana: At a Speed of Life!

ሁለንተናዊ ሰላምና ብልጽግና የሚመጣው ሁሉንም ዓይነት ፈተናዎች እንደየመልካቸው በማሸነፍ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ1 ሺህ 496ኛው ለመውሊድ በዓል በአስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ ሁለንተናዊ ሰላምና ብልጽግና የሚመጣው ሁሉንም ዓይነት ፈተናዎች እንደየመልካቸው በማሸነፍ ነው ብለዋል።

ሀገራችን የገጠሟትን ፈተናዎች በቶሎ ፈትተን ወደምንፈልገው የብልጽግና ምዕራፍ ለመድረስ ቁልፉ በመሥዋዕትነት የታሸ መልካም አገልግሎትን ዛሬውኑ ለመስጠት መቻል ነው ሲሉም አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው እንዳብራሩት፥ ወገኖቻችንን ነፃ ለማውጣት የሚከፈልን መሥዋዕትነት፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመርዳትና ለማቋቋም የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ ሀገራችን በርሀብ እንዳትጠቃ በየማሳው የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ መልካም አገልግሎት ለሕዝቡ ለመስጠት በየቢሮው የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ ሀገራችን በእጅጉ ትፈልጋለች።

የመውሊድ ዕሴቶች ለሀገራችን ዛሬ በእጅጉ እንደሚያስፈልጓት አስታውሰው፤ የምናስበው፣ የምናወራውና የምንሠራው በተስፋችን ላይ ከሆነ ተስፋው ዕውን ሆኖ የምናይበት ጊዜ ቅርብ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

የሀገራችንን የውስጥ ጠላቶች በፍጥነት አሸንፈን የኢትዮጵያን ኃያልነት ማስፈን አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በዲፕሎማሲው ረገድ የገጠመንን ፈተና እውነትንና ጥበብን ይዘን ማሸነፍ እንዳለብንም ተናግረዋል።

የሕዝባችንን የኑሮ ውድነት በላቀ የአመራር ክህሎት ደረጃ በደረጃ መቅረፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አዲሱን መንግሥት በድምፁ ያመጣው ሕዝብና አዲሱን አስተዳደር የመሠረተው መንግሥት ታሪክንና ማኅበረሰብን የሚለውጡ አገልግሎቶች፥ የሕዝብን አኗኗርና አስተሳሰብ የሚለውጡ አገልግሎቶች በእጅጉ ያስፈልጓቸዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በፈተናም ብቻ የተከበበች፥ በተስፋም ብቻ የታጀበች አይደለችም ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለተስፋዋ ከሠራን ተስፋዋ ያሸንፋል፤ ሕዝቡም ከችግሩ ጋር ሳይሆን ከመፍትሔው ጋር መቆም ይገባዋል ብለዋል።

የዛሬውን የመውሊድ በዓል ስናከብር ‹በመሥዋዕትነት የታጀበ፤ ሕዝብን ሊለውጥ የሚችል መልካም አገልግሎት መስጠት› የሚለውን የመውሊድ ዋናውን ዕሴት በማሰብ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታውሰዋል።

መውሊድ አላህ በነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በኩል ለዓለም የሰጠውን በረከት የምናስብበት በዓል ነው ያሉት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፥ የመውሊድን በዓል ስናከብር፥ የሰው ልጆች ለሌሎች የሰው ልጆች እያደረጉ ያሉትን እዝነት ማስታወስ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.