በቻይና የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ31 ሺህ ሲያልፍ ከ600 በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና በውሃን ግዛት በተቀሰቀሰ ኮሮና ቫይረስ የሚያዙ እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
የቻይና ብሄራዊ የጤና ኮሚሽን በዛሬው እለት እንዳስታወቀው በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 636 ደርሷል።
ከዚህ ውስጥ አዲስ የ73 ሰዎች ሞት የተመዘገበ ሲሆን፥ 69ኙ ቫይረሱ በተቀሰቀሰባት ሁቤይ ግዛት መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ትናንት ከነበረው በ3 ሺህ 143 ጭማሪ ማሳየቱን እና አሁን ላይ በአጠቃላይ በቻይና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 31 ሺህ 161 ማድረሱን የኮሚሽኑ ሪፖርት ያመላክታል።
በቻይና በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ፥ በሀገሪቱ የቫይረሱን መቀስቀስ ቀድሞ ያስጠነቀቀው የ34 ዓመቱ ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ አንዱ ነው።
የዶክተሩ ህልፈት በበርካቶች ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፥ የቻይና መንግስትም ምርመራ መጀመሩ ነው የተገለፀው።
በተያያዘም የኮሮና ቫይረስ ከቻይና ውጭ በ25 ሀገራት መታየቱን እና በፊሊፒንስ እና በሆንግ ኮንግ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።
የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም የጤና ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል 675 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንድሚያስፈልግ ገልጿል።
ሀገራትም ለዚህ ስራ ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪውን አቅርቧል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ