Fana: At a Speed of Life!

ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲከናወን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነት እንደሚጠበቅ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊታችን ነሃሴ ወር ላይ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲከናወን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነት እንደሚጠበቅ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መጪውን ሃገር አቀፍ ምርጫ አስመልክቶ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ዕቅዱን በተመለከተ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና የሽግግር ወቅት ፖለቲካ ላይ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ማርሸት ታደሰ፥ ከጊዜ ሰሌዳው ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቅታዊና ሃገራዊ ጉዳዮችን ከግምት ሊያስገቡ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት።

የምርጫው ባለቤት የሆነው ህዝብ ለምርጫው የሚያደርገው የስነ ልቦና ዝግጅት እና  የፓርቲዎች ዝግጅት ሁኔታ ምርጫውን በተባለው ጊዜ ለማከናወን ወሳኝ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል ።

በሌላ በኩል መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ ውብሸት ግርማ በበኩላቸው ፥መንግስት ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ከቻለ ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ስሌዳ ማከናወን ይቻላል ብለዋል፡፡

የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ መልካሙ ኡጎ ደግሞ  የምርጫ ሂደት መርሃ ግብሮችን  በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማስፈጸም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምሁራኑ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ታኣማኒ፣ ፍትሃዊ  እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን በሂደቱ ላይ አሉታዊ  ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ጉዳዮች ዙሪያ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዋናነት ምርጫዉ ከዚህ ቀደም እንዳለፉት ምርጫዎች የችግር ምንጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.