ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ጥቅምት 1 ይጀምራል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዘጋጅነት በየዓመቱ በጥቅምት ወር የሚከበረው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ዘንድሮም ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚከበር ተገለጸ፡፡
ሁለተኛውን የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክቶ የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የዘንድሮው የሳይበር ደህንነት ወር “የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃፊነት ነው! እንወቅ! እንጠንቀቅ!” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልፀዋል፡፡
የመርሃ ግብሩ ዋና ዓላማም የሳይበር ማህበረሰቡን እና ተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና ለማጎልበት የሚያስችል ንቅናቄን በማካሄድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የማስጠበቅ ተልዕኮ ማገዝ መሆኑን ዶ/ር ሹመቴ ገልጸዋል፡፡
በዚህ የሳይበር ደህንነት ወር የዜጎችንና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና ለመገንባት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑም ዶ/ር ሹመቴ ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን የዜጎች ሆነ የተቋማት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከማደጉ ጋር ተያይዞ በዜጎች፣ በተቋማት እንዲሁም በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ፥በተለይም ሀገራችን ባለችበት ወቅታዊ የደህንነት ሁኔታ የጥቃት ዒላማ ልትሆን የምትችልበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከል ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥም ሙያዊ ስነ-ምግባርና ክህሎት የተላበሰ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ትክክለኛ ቴክኖሎጂ መጠቀም እና በህግ ማዕቀፎች መታገዝ መሠረታዊ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ የሳይበር ወርም ከ300 በላይ የሚሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማት እንደሚሳተፉ፣ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሑፎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚካሄዱ ተገልጿል፡፡
የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ እንደሚከበር ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!