የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር ምንድነው?
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የእሰፈፃሚነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመሩት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 74 “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር” ብሎ ያስቀመጣቸው ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፦
1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ ርዕስ መስተዳድር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው፡፡
2. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባሎችን ከሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ወይም ለሥራው ብቃት ካላቸው ሌሎች ግለሰቦች መካከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ያስጸድቃል፡፡
3. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፡፡
4. የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ይወክላል።
5. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣቸውን ፖሊሲዎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ይከታተላል።
6. የሀገሪቱን የውጭ ፖሊሲ በበላይነት ያስፈጽማል።
7. ኮሚሸነሮችን፣ የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንትና ምክትል ኘሬዚዳንትን እና ዋና ኦዲተርን መርጦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ያሰጸድቃል፡፡
8. የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብቃት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
9. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እና 7 ከተዘረዘሩት ውጭ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሲቪል ሹመቶችን ይሰጣል።
10. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው ሕግ ወይም በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ለኘሬዚዳንቱ አቅርቦ ያሰጣል።
11. ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ፣ በመንግሥት ስለተከናወኑ ተግባራትና ስለወደፊት ዕቅዶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየወቅቱ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
12. በዚህ ሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጎች የተሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል።
13. ሕገ መንግሥቱን ያከብራል፣ ያስከብራል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!