ከፖሊስ የሙያ ስነ ምግባር ውጪ በአንዲት ግለሰብ ላይ ድብደባ የፈፀሙ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፖሊስ የሙያ ስነምግባር ውጪ በአንዲት ግለሰብ ላይ ድብደባ የፈፀሙ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ሚካኤል አደባባይ አካባቢ መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ/ም ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ም/ኢ/ር ጃፋር አሊ እና ኮንስታብል መስፍን በተለ የተባሉ የቆሬ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አባላት አንዲትን ግለሰብ በአስነዋሪ ሁኔታ በመደብደባቸው በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ህዝብን በሰብአዊነት ማገልገል የአዲስ አበባ ፖሊስ መርህ መሆኑ እየታወቀ ÷ አንዳንድ አመራሮችና አባላት ግን ይህን መርህ በመተላለፍ የሚፈፅሙት ህገ ወጥ ድርጊት ተቋሙ የማይታገስ መሆኑን ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በ2013 ዓ ም ብቻ በልዩ ልዩ ጥፋት ላይ የተገኙ 171 የፖሊስ አመራሮችና አባላት ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ ማድረጉን ተቋሙ አስታውሷል።
ከስራ ከተሰናበቱት 29ኙ ከሰብአዊ መብት ጥስት ጋር በተያያዘ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።
ህግን በመተላለፍ ጥፋት በሚፈፅሙ አባላት እና አመራሮች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፖሊስ አስታውቆ÷ ህብረተሰቡ እንዲህ ዓይነት ከፖሊስ የሙያ ስነ- ምግባር ውጪ የሆኑ ድርጊቶች በሚፈፀሙበት ወቅት በፍጥነት ጥቆማ እንዲያደርግ እየገለፅን ግለሰቧን በደበደቡ የፖሊስ አባላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ወስዶ ውጤቱን ለህዝብ የሚሳውቅ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን