Fana: At a Speed of Life!

የሩስያና የቱርክ ፕሬዚደንቶች ጠቃሚና ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገለጹ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቱርኩ አቻቸው ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን በሩሲያ ተገናኝተው በሶሪያ ወቅታዊ ሁኔታና በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱ መሪዎች ባካሄዱት ውይይት፥ በሰሜን ምዕራብ የሶሪያ ግዛት አዲስና የተባባሰ ግጭት እንዳያገረሽና ሰላም ማስፈን በሚቻልበት እንዲሁም ሩስያ ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ መሳሪየዎችን ለቱርክ በምትሸጥበት ሁኔታ ላይ ነው በዋነኛነት የመከሩት።

የሩስያው ዜና አገልግሎት ታስ እንደዘገበው፥ ፑቲንና ኤርዶኻን ለሶስት ሰዓት ያህል የቆየ ውይይት ነው ያካሄዱት።

መሪዎቹ ከውይይታቸው በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት የተቆጠቡ ቢሆንም፥ ወደሩስያ በመጓዛቸውና የጋራ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ስላደረጉት ጥረት ፕሬዚደንት ኤርዶኻንን ያደነቁት ፕሬዚደንት ፑቲን፥ ውይይቱ በጣም ጠቃሚና መሰረታዊ ጉዳዮችን አንስተው የተነጋገሩበት መሆኑን አልሸሸጉም።

ፕሬዚደንት ኤርዶኻን በበኩላቸው፥ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከፑቲን ጋር የነበራቸው ውይይት “ውጤታማ” ነበር ብለዋል።

አሸባሪነትን በጋራ መዋጋት በሚችሉባቸው እና በሌሎች ቀጠናዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር ማድረጋቸውም ታውቋል፡፡

ውይይቱ የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ለማሻሻልና ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የሶሪያ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ደግሞ ፥ ፕሬዚደንት ኤርዶኻን የሩሲያ አቻቸውን የሞስኮና የሶሪያ ጦር፥ ኢድሊብ በተሰኘው በሰሜን ምዕራብ የሶሪያ ክልል በሚገኙትና አንካራ በምትደግፋቸው ታጣቂዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽሙና ባለፈው ዓመት ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምምት እንዲተገበር ጠይቀዋል።

በአንድ በኩል ሞስኮ፥ የሶሪያው ፕሬዚደንት በሽር አልአሳድ በጦርነት የተበጣጠሰችውን አገራቸውን አንድ ለማድረግና መልሶ ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት አሜሪካና ሌሎች የውጭ ሃይሎች ባካሄዱባቸው ጣልቃ ገብነትና እንቅፋት ምክንያት ለማሳከት ስላልቻሉ፤ ባደረጉልኝ ኦፊሴላዊ ግብዣ መሰረት ነው ሠራዊቴን ሶረያ ውስጥ ያስገባሁት ትላለች።

ቱርክ በበኩሏ ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነቴን ለመጠበቅ በሚል በሺዎች የሚቀጠር ጦሯን በሰሜን ሶሪያ አሰማርታ የበሽር አል አሳድን ተቀናቃኞች ትደግፋለች።

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፤ የሁለቱ መሪዎች ውይይት ይህን ልዩነት ለማጥበብና ሶሪያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማርገብ በሚቻልበት አግባብ ላይ ያተኮረና ሌሎች የውጭ ሃይሎች ቀጠናውን እንዳያምሱት በጋራ ለመከላከል ይጠቅማል።

ፕሬዚደንት ኤርዶኻን በአሜሪካ የሚደገፍ ነው ያሉትን በሶሪያና በአፍጋኒስታን የሚካሄደውን የሽብር እንቅስቃሴ በሚመለከት ከሩሲያው አቻቸው ፑቲን ጋር ለመምከር ጭምር ነው ወደ ሩስያ ያመረሩት።

በአሜሪካ የሚመራው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆነችው የቱርክ ፕሬዚደንት ለአገራቸው መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፥ አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ አሸባሪነትን መዋጋት ሲገባት በግልጽ “የአሸባሪ ድርጅቶች ድጋፊ ሆናለች” ነው ያሉት።

ለአብነትም ህገ ወጥ የሆነው የኩድርስታን ሠራተኞች ፓርቲ አፍቀሪ የሆነውንና በሰሜን ሶሪያ የሚንቀሳቀሰውን ዋይ ፒ ጂ የተሰኘውን አሸባሪ ቡድን አሜሪካ እንደምትደግፈው ነው ኤርዶኻን የሚገልጹት።

ቱርክ ለሚሳይል መከላከያ የሚውሉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ከሩሲያ የገዛች ሲሆን፥ በቀጣይም ሌሎች መሳሪያዎችን እንደምትገዛ አስታውቃለች።

ፕሬዚደንት ኤርዶኻን በቅርቡ ለንባብ በበቃውና የመሰረታዊ ለውጥ አቀንቃኝ በሆነው መጽሐፋቸው፥ በተወሰኑ አገራት ፍላጎት የሚመራውን የተባበሩት መንግስታትን “የተሻለ ፍትህ የሰፈነበት ዓለም” ማድረግ እንደሚያስፈልግና እንደሚቻል በአጽንኦት መግለፃቸው ይታወቃል።

ምንጭ፦ ታስ፣ አርቲና ሬውተርስ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.