Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን አስፈፃሚ አካላት እንደገና ለማቋቋም ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅ አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የክልሉ ምክር ቤት 18ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን መንግስት አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋምና ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

የክልሉ ፕላን ኮሚሽነር አቶ በድሉ ድንገቱ አዋጁን ዛሬ ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ የተጀመረውን ለውጥ ሊያስቀጥል በሚችል መልኩ የአስፈፃሚ ተቋማቱ እንደገና እንዲቋቋሙ ተደርጓል።

መንግስታዊ ተቋማቱን እንደገና መልሶ ማደራጀት ያስፈለገው ክልላዊና ሀገራዊ ለውጡን የሚመጥን አደረጃጀት በመፍጠር የክልሉን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን በማሰብ መሆኑንም አስረድተዋል።

“ይህም ስራን በብቃት በመምራት በኩል የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በመሙላት የሥራ ድግግሞሽን ለማስቀረት ያስችላል” ብለዋል።

የክልሉን ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው ያመለከቱት።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በክልሉ ቁጥራቸው 54 ተቋማት የነበሩትን እንደገና እንዲደራጁ መደረጉን ገልጸዋል።

አደረጃጀቱ ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመውሰድና ከፌዴራል ተቋማት ጋር ያለውን አደረጃጀት ታሳቢ በማድረግ የተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። “በዚህም የክልሉ አስፈፃሚ ተቋማት እንደገና በ23 ተቋማት እንዲደራጁ ተደርጓል” ብለዋል።

የአስፈጻሚ አካላት እንደገና መደራጀት ክልሉን በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና አስተዳደር ክላስተሮች ለይቶ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመምራት የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደገና የተደራጁት ተቋማት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
1- ግብርና ቢሮ
2- ኢንዱትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ
3- ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ
4- ቱሪዝም ቢሮ
5- ገንዘብ ቢሮ
6- ፍትህ ቢሮ
7- ፕላንና ልማት ቢሮ
8- ስቪል ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ኮሚሽን
9- ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
10- ገቢዎች ቢሮ
11- የመሬት ቢሮ
12- የውሃና ኢነርጂ ቢሮ
13- የማዕድን ቢሮ
14- የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ
15- የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ
16- ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ
17- ጤና ቢሮ
18- ትምህርት ቢሮ
19- ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ
20- የስራ ፈጠራና ስልጠና ቢሮ
21- የመንገድ ቢሮ
22- የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ እና
23- የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ናቸው።

የክልሉን መንግስት አስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋምና ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅም ጉባኤው ከተወያየበት በኋላ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን ኢዜአ ዘግቧል።

ምክር ቤቱም ዛሬ ባካሄደው አምስተኛ ዙር ሰባተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ጉባኤ የ2013 ተጨማሪ በጀት እና የ2014 የክልሉን ጠቅላላ በጀት በማፅደቅ የአምስት ዓመት ቆይታውን አጠናቆ ተሰናብቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.