የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የድጋፍ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ ይገኛሉ።
የችግሩ ሰለባ ለሆኑ የማህበረሰበ ክፍሎች አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ ከአዲስ አበባ እና ከክልሎች የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤቶች የተወጣጣ የእርዳታ አሰባሳቢ ጥምር ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል።
ኮሚቴው ከነገ ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በሃይማኖት አባቶች በሰሜኑ ኢትዮጵያ ያለው ችግር በሰላም እንዲፈታ በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካ አስታውሰው÷ ለሃገር የሚበጀው ሰላም እና አንድነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ በምድርም በሰማይም የተወደደ ተግባር በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የሌሎች እምነት ተከታዮችም መልካም መስራት የሚያስገኘውን ከፍተኛ ዋጋ በመገንዘብ ድጋፍ እንዲያድርጉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
እርዳታውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ፣ በአዋሽ ባንክ፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እና በአቢሲኒያ ባንክ ገቢ ማድረግ እንደሚቻል በመግለጫው ተመላክቷል።
አሁን ላይ ድጋፉን በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ በተከፈተው የሂሳብ ቁጥር 1000091319997 ገቢ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸው÷ በሌሎች ባንኮች የተከፈቱ የሂሳብ ቁጥሮች በቀጣይ ይፋ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!