በሲንጋፖር የሮቦት ፖሊሶች ስራ ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሲንጋፖር ራስ ገዝ ሮቦቶች በመጠቀም በከተማይቱ ልዩ ልዩ ያልተፈለጉ ማሕበራዊ ባህሪያትን የመቆጣጠር ሙከራ እያከናወነች መሆኗ ተገለፀ፡፡
ዣቨር የተሰኙት ሮቦቶቹ 360 ዲግሪ መመልከት የሚያስችል ካሜራ ያላቸው እንደሆኑና የሚመለከቱትን ነገር በመተንተን ጥሰቶችን እንዲለዩ የሚያስችል ሴንሰር የተገጠመላቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ሮቦቶቹ ያልተፈለጉትን ማሕበራዊ ባህርያት በሚመለከቱበት ጊዜ ወደ ቁጥጥር ማዕከሉ መረጃ በመላክ ፖሊሶች በግንባር ተገኝተው÷ አልያም በሮቦቱ በኩል እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል ነው የተባለው፡፡
አምስት ያህል የሃገሪቱ ተቋማት ተሳታፊ የሆኑበት ይህ ሙከራ ፖሊሶች የግድ ለሁሉም ጉዳይ በአካል ለመገኘት እንዳይገደዱና ስራዎችም በተሻለ መልኩ እንዲሰሩ ያስችላል ተብሎለታል፡፡
ሮቦቱ ቁጥጥር የሚያደርግባቸው ያልተፈለጉ ማሕበራዊ ባህርያትም በተከለከለ ቦታ ማጨስን ጨምሮ ሕገ-ወጥ ንግድ፣ አግባብ ባልሆነ መልኩ ብስክሌቶችን ማቆም፣ የኮቪድ19 ደንብን መጣስ፣ ለአምስት ወይም ከዚያ በላይ መሰብሰብ እንዲሁም በእግረኛ መንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች መሆናቸው ነው የተገለፀው፡፡
ሲንጋፖር ከዚህ ቀደም በህዝባዊ መናፈሻዎች ውስጥ የኮቪድ 19 ሕግጋት መጣስ አለመጣሳቸውን በሮቦቶች አማካኝነት ለመቆጣጠር ሙከራ አድርጋ ነበር፡፡
ለሙከራውም በቦስተን ዳይናሚክስ አማካኝነት የተፈበረኩ ከ1 ሜትር በታች ተቀራርበው በተገኙ ሰዎች ላይ እንደ እውነተኛ ውሻ የሚጮሁ የሮቦት ውሻዎችን ተጠቅማ እንደ ነበር ተመላክቷል፡፡
በሮቦቶቹ ተመሳሳይ የፖሊስ ስራዎችን የመስራት ሙከራ በአሜሪካንም ተከናውኖ የነበረ ሲሆን÷ በኒውዮርክ ከተማ ከህዝብ በገጠመው ተቃውሞ ምክንያት ሙከራው ሊቋረጥ መቻሉን ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስትቲዩት ቴክስፕሎርን ጠቅሶ ያጋራው መረጃ ያመላክታል፡፡