የአሸባሪው ቡድን ቤቶች ላይ ከባድ መሳሪያ ጭምር በመተኮስ ነዋሪው እንዲሸሽ አድርጓል
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የአሸባሪው ሀወሓት ቡድን ደብረ ዘቢጥ ከተማን ሙሉ ለሙሉ በያዘበት ወቅት ቤቶች ላይ ከባድ መሳሪያ ጭምር በመተኮስ ነዋሪው እንዲሸሽ ማድረጉ ተገለጸ::
ወይዘሮ ዘውዲቱ ጎበና በሰሜን ወሎ ዞን የመቄት ወረዳ ደብረ ዘቢጥ ከተማ ነዋሪ ናቸው::
አሸባሪው ቡድን ከተማዋን በመውረሩ ሀብት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ቆላማ አካባቢ ባሉ ዘመዶቻቸው ተጠግተው እንደነበር ይናገራሉ::
የእርሳቸው ባለቤት ከቀናት በኋላ ወደ ቀዬው ተመልሰው ስንቅ ሊያመጡ ሲሉ በአሸባሪዎች እንደተገደሉባቸውም ይገልጻሉ::
ለስንቅ ብለው የወጡትን ባለቤታቸውን በጥይት በማጣታቸው ወደ መኖሪያቸው ተመልሰው ኀዘን ተቀምጠዋል::
ለወትሮ ቢሆን በሃዘንም በደስታም በሰዎች የሚሞላው ቤታቸው ወና ሆኗል::
ብዙዎች ከከተማዋ ለቀው ስለወጡና ስላልተመለሱ የኀዘን ተካፋይ ማግኘት አለመቻላቸውን ኢፕድ ዘግቧል::
ከውስን ቤተሰቦቻቸው ጋር በባዶ ቤት ሆነው የአሸባሪውን በደል በማስታወስ ሃዘናቸውን ይገልጻሉ::
ይህ ክፉ ጠላት ሀብትና ንብረት መዝረፉና ማውደሙ ሳያንስ የንጹሀንን ነፍስ እንዳሻው ሲያጠፋ እንደነበር ወይዘሮ ዘውዲቱ ይናገራሉ::
ዛሬ ላይ ቤተሰቦቻቸው ዘመድ ቤት ቢሆኑም ወቅቱ እንኳንስ ዘመድ አስጠግቶ ማኖር ይቅርና የራስን ቤተሰብም ለመምራት አስቸጋሪ ነው በማለት፤ አሸባሪ ቡድን ያደረሰውን በደል መቼውንም አንረሳውም ብለዋል::
በደብረ ዘቢጥ ከተማ ወይን ሰፈር ነዋሪ የሆኑት ቄስ መርሻ ብርሃኔ እንደሚሉት፤ የአሸባሪው ሀወሓት ቡድን ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ በያዘበት ወቅት ቤቶች ላይ ከባድ መሳሪያ ጭምር በመተኮስ ነዋሪው እንዲሸሽ አድርጓል::
እያንዳንዱ ነዋሪ ሸሽቶ በመውጣቱ የግለሰቦችን ቤት እንደ መኖሪያ ሲጠቀሙበት ነበር::
ቤት ውስጥ ያለውን ከዱቄት እስከ ቁም ከብት ያገኙትን ዘርፈው በልተዋል::
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!