ጥረት ኮርፖሬት በነፋስ መውጫ ከተማ ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥረት ኮርፖሬት በአሸባሪው ህወሓት ቤት ንብረታቸው ተዘርፎ ለችግር ለተጋለጡ የነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪዎች ድጋፍ አደረገ።
400 ኩንታል ዱቄት እና 2 ሺህ ሊትር ዘይት ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፥ ይህም ድጋፍ በገንዘብ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑን የጥረት ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አምላኩ አስረስ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ዛሬን ጨምሮ በቀጣይ ቀናት ለመቄት ወረዳ አካባቢዎች በኮርፖሬቱ ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል።
አሸባሪው ቡድን ጉዳት ያደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና የእለት ደራሽ ድጋፍ ስራዎች የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል ዶክተር አምላኩ።
ጥረት የክልሉ ህዝብ ሀብት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ ባለፉት 9 ወራት ብቻ ለሰራዊቱና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ገንዘብ እና ሎጅስቲክስ በአጠቃላይ 100 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
ትውልዳቸው በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ግለሰብ አቶ ይበልጣል አዳምጤም በተመሳሳይ ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል።
ግለሰቡ 300 ሺህ ብር ወጭ የተደረገበት 50 ኩንታል ዱቄት እና 2 መቶ ሊትር ዘይት ነው ድጋፍ ያደረጉት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ፥ አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡ የእለት ጉርስ እንኳን እንዳይኖራቸው አድርጎ መሄዱን ተናግረዋል።
በዞኑ ቡድኑ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች እስከ 65 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ለችግር ተጋልጠዋል የእለት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋልም ነዉ ያሉት።
የልማት ድርጅቶች የህዝብ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት እና ለህዝብ የሚደርሱበት አሁን ነው ያሉት አቶ ቀለመወርቅ፥ የመንግስት ተቋማት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና በጎ አድራጎት ላይ የተሰማሩ ሁሉ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፤ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል ።
በዙፋን ካሳሁን
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!