Fana: At a Speed of Life!

ሶማሊያ በበረሃ አንበጣ መንጋ መስፋፋት ብሄራዊ የአደጋ ስጋት አዋጅ አወጀች

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መስፋፋቱን ተከትሎ ሶማሊያ ብሄራዊ የአደጋ ስጋት አዋጅ አወጀች።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።

ሶማሊያም ብሄራዊ የአደጋ ስጋት አዋጅን በማወጅ በቀጠናው የመጀመሪያዋ ሃገር ሆናለች።

የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር በርካታ መጠን ያለው ሰብልን የሚያወድመው የበረሃ አንበጣ በሶማሊያ የምግብ ዋስትና ላይ አደጋ ደቅኗል ሲል ገልጿል።

አሁን ላይ በሶማሊያ ያለው ያልተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት በማድረግ የበረሃ አንበጣውን ለመከላከል የሚደረገተውን ጥረት አዳጋች አድርጎታል ነው የተባለው።
የአንበጣ መንጋውን ምርት ከሚሰበሰብበት ሚያዚያ ወር በፊት መቆጣጠር አይቻልም የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ባለፉት 25 አመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን መግለጹ አይዘነጋም።

በሌላ በኩል በጎረቤት ኬንያ ባለፉት 70 ዓመታት መሰል የአንበጣ መንጋ ተከስቶ እንደማያውቅ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) አስታውቋል።

ድርጅቱ ለአንበጣ መንጋው ዓለም አቀፍ ትብብር ይደረግ ዘንድ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል።

ከፍ ያለ ውድመት እያደረሰ ያለውን መንጋ ስርጭት መቆጣጠር ካልተቻለም እስከ ፊታችን ሰኔ ወር ድረስ የአንበጣ መንጋው 500 እጥፍ ይሆናል ሲልም አስጠንቅቋል።

ምንጭ፦ ቢ.ቢ.ሲ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.