Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት አራት ዓመታት በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የድርቅ አደጋ ስጋትን መቀነስ መቻሉ ተገለጸ

በአዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የድርቅ አደጋ ስጋትን በመቀነስ በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በእነዚህ ዓመታት ከ58 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በህብረተሰብ ተሳትፎ ተከናውኗል።
 
ባለፉት አራት አመታት የተጀመረው ህብረተሰቡን ያሳተፈ የበጋ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ካስገኘው ውጤት ባሻገር ለኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ እውቅናን አትርፏል።
 
በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሰራው ስራ የተፈጥሮ ሃብትን ከመጠበቅ፣ የህብረተሰብ ኑሮን ከመደገፍና አብሮ የመስራት ባህልን ከማጎልበት አንጻር በርካታ ጥቅሞች ማስገኘቱን ተጠቁሟል።
 
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ እንደገለጹት፥ በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚካሔደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ የውሃ አማራጮችን በማሳደግና በማበልጸግ ለመስኖ ልማት መስፋፋት ጉልህ ሚና አበርክቷል።
 
ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ምንም ዓይነት የእጽዋት ሽፋን የማይታይባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የእጽዋት ሽፋን ተስተውሎባቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ የሰብል ምርትና የግጦሽ ሳር እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል።
 
ቀደም ሲል በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ይገኝ ከነበረው ምርት በትንሹ አንድ ኩንታል ጭማሪ ማግኘት መቻሉን በየሁለት አመቱ በሚደረገው የተጽዕኖ ግምገማ ሪፖርት ላይ መታየቱን ገልጸዋል።
 
ባለፉት አራት ዓመታት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች 58 ቢሊየን ብር የሚያወጣ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በዘንድሮው የበጋ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ስራ መጀመሩን ተጠቁሟል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.