Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት 7 ሺህ ትምህርት ቤቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት 7 ሺህ ያህል ትምህርት ቤቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።

ይህ የተገለፀው ሀገር አቀፍ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

የትምርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ አሸባሪው ቡድን በትግራይ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችንና ከ48 ሺህ በላይ መምህራንን ከትምህርት ስርዓት ውጭ አድርጓል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ተማሪዎችን ወደ ጦርነት እየማገደ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን ግጭቶችን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በማስፋፋት ትምህርት ቤቶችን አውድሟልም ነው ያሉት።

ባለፈው አንድ ወር ብቻ በአፋር ክልል 88 ሺህ ተማሪዎች ይማሩ የነበሩባቸው 455 ትምህርት ቤቶች በአሸባሪው ቡድን መውደማቸውን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ደግሞ 140 ትምህርት ቤቶችና ሁለት የመምህራን ኮሌጆች ሙሉ በሙሉና በከፊል መውደማቸውን አስረድተዋል።

በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የውጭ አጋር ድርጅቶችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ሽብርተኛው ህወሓት ተማሪዎችን ለውትድርና በመመልመል ከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ነው የገለጹት።

አፈ ጉባኤው ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ የከፈተውን ጥቃት በማያዳግም መልኩ በመፍታ አካባቢዎቹን በአጭር ጊዜ ወደልማት ማስገባት ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የትምህርት ዘርፉን የማዘመንና የማሳደግ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የ2013 አመት ምህረት የትምህርት ዘርፍ አፈጻጸምና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበዋል።

እስከ ነገ በሚቆየው ጉባኤ ላይ የተለያዩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል።

በአፈወርቅ እያዩ፣ ሃይለኢየሱስ ስዩም እና ሃበነዮም ሲሳይ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.