Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ያሰለጠናቸው 720 የፖሊስ አባላት አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለሰባት ወራት በቦንጋ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን 720 የሚደርሱ ሰልጣኝ ፖሊሶችን አስመረቀ።

በቦንጋ የስልጠና ማዕከል የሰለጠኑት እና በዛሬው እለት የተመረቁት የፖሊስ አባላት ለሰባት ወራት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠናዎችን ያጠናቀቁ መሆናቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ አታርፋ ሙስጠፋ፥ ህግና ስርዓት መሬት ወርዶ እንዲተገበርና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በስነ ምግባር የታነፀ የፀጥታ ሀይል ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የፖሊስ ተልዕኮ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ማስከበር እና ህዝቡን ከጥቃት መጠበቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ተመራቂዎችም የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

መንግስት የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና የለውጡን ጉዞ ከዳር ለማድረስ የፀጥታ ኃይሉን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተወካይ ኮማንደር ኡቻን ኡማን በበኩላቸው፥ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣና የህግ የበላይነት እንዲከበር በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስ አካላት ሚና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ከመስጠት ባሻገርም ተቋሙን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የህግ የበላይነትን በማስከበር ለውጡን ለማስቀጠል መስራት እንደሚገባቸው አብራርተዋል።

የፖሊስ አባላቱ ሙያው የሚጠይቀውን ስነ ምግባር በመላበስና በብቃት በመወጣት ሀገራዊ ለውጡን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ሊያሸጋግሩ እንደሚገባ ጠቅሰው ተመራቂዎችም በስልጠናው ቆይታቸው ያገኙትን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.