Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሁለት ወራት 373 የሽብርተኛው ሸኔ አባላት ተደምስሰዋል

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ባለፉት ሁለት ወራት 373 የሽብርተኛው ሽኔ አባላት መደምሰሳቸውን ገለጸ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በወቅታዊ የክልሉ የሰላም ጉዳይና የአሸባሪው ሸኔ እንቅስቃሴን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ ፖሊስ ባለፉት ሁለት ወራት አሸባሪው ሸኔ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰንዝሯል።

የፌዴራል መንግስት የተኩስ አቁም በመወሰን የአገር መከላከያ ሰራዊት መቐለን ለቆ ከወጣ በኋላ ከአሸባሪው ሕወሓት በሚሰጠው ተልዕኮ መሰረት አሸባሪው ሸኔ በንጹሃን ላይ ግዲያ እየፈፀመ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መዝረፉንና ማውደሙንም ጨምረው ገልጸዋል።

አሸባሪው ሸኔ በነዚሁ አካባቢዎች በየቀኑ ከ2 ሺህ እስከ 3 ሺህ ንጹሃንን ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ ሲሆን፤ የጸጥታ አካላትም ተፈናቃዮችን በመመለስና በመጠበቅ እንዲጠመዱ አድርጓል ነው ያሉት።

በመሆኑም የክልሉ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በሽብር ቡድኑ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸው ባለፉት ሁለት ወራት 373 የቡድኑ አባላት ተደምስሰዋል ብለዋል።

በዘመቻው 273 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና ከ15 ሺህ በላይ ጥይቶችን ከአሸባሪው አስጥለናልም ነው ያሉት።

የጸጥታ አካላት ይህን ሁሉ ዋጋ እየከፈሉ እያሉ አንዳንዶች ‘የጸጥታ አካላት ስራ ላይ እንደሌሉ” በማስመሰል የሚያናፍሱት ወሬም ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

የክልሉ ወጣቶች ከሽብር ቡድኑ ጋር በመፋለምና ለፀጥታ ሃይሎች ትብብር በማድርግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኮሚሽነር ጀነራሉ ማሳሰባቸውን ኦቢኤን ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.