Fana: At a Speed of Life!

ለአሸባሪው ህወሓት ሲሰሩ በነበሩ 27 የሰራዊት አባላት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ችሎት ተሰየመ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለአሸባሪው ህወሓት ሲሰሩ በነበሩና ክስ በተመሰረተባቸው 27 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት በደቡብ ዕዝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ችሎት ተሰየመ።

የኢፌዴሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 293 ንኡስ አንቀጽ አንድን  በመተላለፍ የሀገር መከላከያ ተቋምን የአገልግሎት ደንብ በመጣስ እንዲሁም አንቀጽ 32 ንኡስ አንቀጽ አንድ (ሀ) እና አንቀጽ 247(ሐ) ሰራዊቱ ወደ ጠላት እንዲኮበልል በማደፋፈርና በማነሳሳት ኮሎኔል ካሳ ሀብቱ፣ ኮሎኔል ሀጎስ አሰፋና ሌተናር ኮሎኔል ሀይላይ ገብሩ በዋና ወንጀል አድራጊነት  ክስ የተመሰረተባቸው ይገኙበታል።

ተከሳሾቹ የገቡትን ቃል ኪዳን ወደጎን በመተው የሰራዊቱን እንቅስቃሴ አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ሲያከናውኑ መቆየታቸው በችሎቱ ተነስቷል።

የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ምስጢራዊ ሰነዶች ለትግራይ ልዩ ሃይል አሳልፈው በመስጠት፣ የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ትጥቆች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ምስጢራዊ ቡድን በማደራጀትና መሳሪያዎቹን በማበላሸት ስራ ላይ ተጠምደው እንደነበር በችሎቱ ተገልጿል።

ተከሳሾቹ ለግዳጅ የተዘጋጁ መሳሪያዎች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ፣ ሰራዊቱ ሽብርተኛውን የሸኔ አባላትን ለመደምሰስ በሚንቀሳቀስበት ዕለት ቀድሞ መረጃ በመስጠትና ተልዕኮው ተፈላጊውን ውጤት እንዳያገኝ በማድረግ፣ የሰራዊቱን ምስጢራዊ ክንዋኔዎች ለሽብርተኛው አካል ማድረስም የፈፀሙት የወንጀል ተግባር መሆኑ ችሎቱ ተመልክቷል።

የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ወደጎን በመተው ከሽብርተኛው አካል የሚሰጣቸውን ድብቅ አጀንዳ መፈፀም በሚያስችላቸው አካሄድ ላይ ብቻ ማተኮር፣ የትግራይ ልዩ ሃይሎች “የብልፅግና ወታደሮችን” ድል እያደረጉ ነው የሚል ሽብር መንዛትም ጥፋተኛ ያስባላቸው መሆኑ ተመልክቷል።

በዚህም ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በ24 መዝገብ በተከሰሱ  27 የሰራዊቱ አባላት ላይ በደቡብ ዕዝ መምሪያ የተሰየመው ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዛሬ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.