Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት በፈጸመው ጥቃት በአፋርና አማራ ክልል ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር እና የብሄራዊ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባሪያ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ህወሓት በፈጸመው ጥቃት በአፋርና አማራ ክልል ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገለጹ።

በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በሰብአዊ ድጋፍ እየተንቀሳቀሱ ላሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አጋር አካላት በሰብአዊና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ሚኒስትሯ በዚህ ወቅትመንግስት ወደ ትግራይ የሚያስገቡ አራት መንገዶችን ሲጠቀም የነበረ ቢሆንም ህወሓት በከፈተው ጥቃት መስመሮቹ መዘጋታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም መንግስት በእነዚህ መንገዶች ያደርስ የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲቋረጥና በአካባቢው ያለው ሰብአዊ ቀውስ እንዲባባስ ማድረጉን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል ወደ ትግራይ ክልል የሚያስገባ መስመር ቢኖርም አሸባሪው ቡድን ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችንና ንጹሃን ዜጎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት እየፈጸመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።

እስካሁን ከህልውና ዘመቻው ወዲህ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ለሰብአዊ ቀውስ መዳረጋቸውን አንስተዋል።

በአማራ ክልል ብቻ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁመው፥ አሁን ላይ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

መንግስት በትግራይ ክልል በ47 ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት አድርጓልም ብለዋል ሚኒስትሯ።

ከዚህ ባለፈም እስካሁን ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ 321 ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.