Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት በነፋስ መውጫ የሚገኘውን የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ዘርፎ የጥበቃ ሠራተኛውን ገድሎ ሄዷል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በነፋስ መውጫ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ዘርፎና አውድሞ የጥበቃ ሠራተኛውን ገድሎ ሄዷል፡፡

በጋይንት ነፋስ መውጫ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገብርዬ ቅርንጫፍ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሙሉ ለሙሉ ተዘርፎ መውደሙን የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለምነው ስዩም ገልጸዋል፡፡

የባንኩ የጥበቃ ሠራተኛ እንደተገደለም አስታውቀዋል፡፡

አቶ አለምነው በሥፍራው ለሚገኙት የጋዜጠኞች ቡድን እንደገለጹት÷ አሸባሪው ህወሓት ባንኩን በመሳሪያ በመደብድብ የኤቲ ኤም ማሽኑን ጨምሮ የባንኩን ቋሚ ሀብቶች ሙሉ ለሙሉ አውድሟል፡፡

የአሸባሪው ታጣቂዎች የዘረፉትን ገንዘብ ሳይጨምር ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የሀብት ኪሳራ አድርሰዋል ነው የተባለው፡፡
አቶ አለምነው እንዳሉት÷ አሸባሪው የተቋሙንና የግለሰቦችን መረጃ የያዙ ፋይሎችን፣ ኮምፒዩተሮችን፣ የዳታ ሰርቨሩን፣ ጠረጴዛና ወንበሮችን ጨምሮ አጠቃላይ የባንኩ ንብረት ላይ ኪሳራ አድርሷል፡፡

ቋሚ ንብረቶችን ከማውደሙ በተጨማሪ ካዝና ውስጥ ከነበረው ገንዘብ ውጭ በኤቲ ኤም ማሽን ውስጥ ያለውንም ሰብሮ መዝረፉን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ወደ 4 ሺህ የሚሆኑ የደንበኛ ፋይሎች ከጥቅም ውጭ እንደሆኑ አስታውሰው÷ ወጪና ገቢ የተደረጉ የመረጃ ዶክመንቶችም አገልግሎት በማይሰጡበት ደረጃ ተበታትነው እንደጠፉ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ዝርፊያ ለማድረስ በርካታ ቁጥር ያላቸው ህጸናትን ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደነበርና የመከላከያ ሠራዊትና የልዩ ሀይል አባላት በፈጸሙት ተጋድሎ አካባቢውን ማስለቀቅ እንደተቻለም አቶ አለምነው ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የነፋስ መውጫ ከተማ ሙሉ ለሙሉ ከአሸባሪው ነጻ ወጥታ ማህበረሰቡ ሠለማዊ ኑሮውን ለመምራት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.