Fana: At a Speed of Life!

ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ አካላት በህግ ሊጠየቁ ነው

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 62 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሰራተኞች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የፀረ-ሙስና ህግ ምክር፣ ትግበራና ልምድ ቅመራ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ጋሻው እንደገለፁት ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑት 16 የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኒቨርሲቲና 46 የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች ናቸው፡፡

ማንኛውም የመንግስት ተሿሚ፣ የህዝብ ተመራጭ እና የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርቶች እንዲሁም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች የቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን ማስመዝገብ እንዳለባቸው ቢደነገግም ህጉን የሚተላለፉ በመኖራቸው ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ሀብትን አለማስመዝገብ እና ሆን ብሎ የተሳሳተ መረጃ መስጠት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ 881/2007 አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት በሙስና ወንጀል ህግ ያስጠይቃል ብለዋል፡፡

ይህንን በማስመልከትም ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት የሰጠውን የሀብት ማስመዝገብ የጊዜ ገደብ ተጠቅመው ለማስመዘገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ አካላትን መረጃና ማስረጃ በማጠናቀር የመክሰስና የመመርመር ሥልጣን ለተሰጣቸው አካላት ለመላክ የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.