Fana: At a Speed of Life!

ዶናልድ ትራምፕ አዲሱን የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ ይፋ አደረጉ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱን የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ ይፋ አደረጉ።

ትራምፕ የሰላም እቅዱን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ይፋ አድርገውታል።

በአዲሱ የሰላም እቅድ የፍልስጤማውያን ሉዓላዊ ግዛት እንዲመሰረት ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

ከዚህ ባለፈም ዌስት ባንክ የእስራኤል ሉዓላዊ ግዛት መሆኗን በእቅዳቸው ይፋ አድርገዋል።

የፕሬዚዳንቱ እቅድ የእስራኤልና ፍልስጤም የግጭት መንስኤ የሆነችው እየሩሳሌም ከተማን የእስራኤል አይነኬ ከተማ አድርጎ የሚያስቀጥል ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የትራምፕ እቅድ ፍልስጤማውያንም ሆኑ እስራኤላውያን አሁን ላይ ከሚኖሩበት ስፍራ ወይም መኖሪያ ቤት እንደማይለቁ ያመላክታል።

ይህም አሁን ላይ እስራኤል በዌስት ባንክ ያስጀመረችው የሰፈራ ፕሮግራም ዘላቂነት እንዳለው ማሳያ ነው ተብሏል።

ትራምፕ አዲሱ እቅድ ለፍልስጤማውያን የሚበጅና የመጨረሻው የሰላም አማራጭ መሆኑንም አስታውቀዋል

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም በእቅዱ ዙሪያ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመምከር ወደ ሞስኮ ያቀናሉ ነው የተባለው።

ፍልስጤማውያን በበኩላቸው የትራምፕን እቅድ ተቃውመው በራማላህ ቁጣቸውን ገልጸዋል።

“ፍልስጤምን ያለ ምስራቅ እየሩሳሌም ማሰብ አይቻልምም” ነው ያሉት ሰልፈኞቹ።

የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስም የትራምፕን እቅድ ተቀባይነት የሌለውና “ሴራ” ሲሉ ገልጸውታል።

አባስ በንግግራቸው እየሩሳሌምም ሆነች የፍልስጤማውያን መብትና ነጻነት ለድርድር የማይቀርቡና የማይሸጡ ናቸው ብለዋል።

የዓረብ ሊግ በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ለቅዳሜ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ታውቋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.