በሊቢያ እየተባባሰ የመጣው ግጭት የ636 ሺህ ስደተኞችን ህይወት ለአደጋ ማጋለጡ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 19 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በሊቢያ እየተባባሰ የመጣው ግጭት የስደተኞችን ህይወት የበለጠ አስጊ ማድረጉ ተነገረ፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በሊቢያ እየተባባሰ ያለው ጦርነት የ636 ሺህ ስደተኞችን ሕይወት ከፍተኛ አደጋ ላይ መጣሉን ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ ባለፈ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ቀውስ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ሀገራት ለማቋረጥ የሚጥሩ ስደተኞች ህይወትንም አደጋ ጥሏል፡፡
ባለፈው ሐምሌ ወር በሊቢያ በሚገኝ የስደተኞች ማቆያ ማእከል ላይ በተፈፀመ የአየር ጥቃት የተገደሉትን 50 ሰዎች በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ መረጃ አውጥቷል፡፡
ከሙዓመር ጋዳፊ ህልፈተ ህይወት በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች የሚገኘው ሊቢያ በፓለቲካ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቅውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡
ለዚህ ቀውስም መቋጫ ለመስጠት በሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን እና በቱርክ አቻቸው ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን አደራዳሪነት ከዚህ ወር በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ተደርጎ እንደነበረ ተጠቁሟል፡፡
ነገር ግን ሀገሪቱን ለሁለት በክፈል እየመሯት በሚገኙት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈው የፋይዝ አል ሲራጅ እና በጄኔራል ከሊፋ ሀፍታር ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት እያለፈ መሆኑ ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅትም በሊቢያ የእርስ በርስ ጦርነት የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች እና የውጭ ኃይሎች እየተሳተፉ እንደሆነ ይነገራል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የስደተኞች ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ጄፍ ክሪስፕ ግጭቱ እየባሰ የሚሄድ ይመስላል ፤ ይህም የስደተኞችን ሕይወት የበለጠ አስጊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ምንጭ፡- አልጀዚራ