ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ የተሰኘ የቱሪዝም መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ጥር 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ50 በላይ የኬንያ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚዎች የተሳተፉበት ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ የተሰኘ የቱሪዝም መድረክ በኬንያ ተካሄደ።
መድረኩ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በናይሮቢ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አማካኝነት የተዘጋጀ ነው።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አስጎብኚዎች እና የጉዞ ወኪሎች፥ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ለማድረግ መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅና ለማሻሻጥ መስማማታቸው ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ የጎብኚ መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ በሚያደርጉት ተሳትፎ መጠን የሚያገኙትን ጥቅም እና የኢትዮጵያ የመስህብ ስፍራዎችን በተመለከተም ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት 40 ሺህ የሚሆኑ ኬንያውያን ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል፤ ሚሲዮኑ ይህን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎችን መታደላቸውን ያነሱት አምባሳደሩ፥ በሃገራቱ አስጎብኚ ድርጅቶች መካከል ትስስር እንዲኖር ኤምባሲው ይሰራል ብለዋል።
“ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ” የተሳተፉ የኬንያ አስጎብኚዎች እና የጉዞ ወኪሎች በስድስት ወራት ውስጥ በድጋሚ ተገናኝተው አፈፃፀማቸውን በመገምገም የተሻለ ስራ ለማከናወን መስማማታቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።