በስፖርት ውርርድ ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመጣው የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄደ።
በኢፌዴሪ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ባዘጋጀው መድረክ ላይ በስፖርት ውርርድ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
በጥናቱ የስፖርት ውርርድ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መምጣቱ ተነስቷል።
በመድረኩ ላይ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በጥናቱ ላይ የቀረበ ሲሆን፥ ኡጋንዳ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወጣቶቻቸው የዚህ ሰለባ በመሆናቸው የስፖርት ውርርድን ማገዳቸው ተጠቅሷል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 160/2001 መሰረት የስፖርት ውርርድ ከሎተሪ ጨዋታ አይነቶች አንዱ መሆኑ ቢደነገግም፥ ከውርርድነት ወደ ቁማርነት እየተቀየረ መምጣቱም ተገልጿል።
አሁን ላይም በኢትዮጵያ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ቀውሶችን እያስከተለ መሆኑም ነው በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ የተነሳው።
ከኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንፃር ሲታይ የሀብት ብክነት እና የኑሮ መዛባት ተጠቃሽ መሆናቸውም ነው የተገለፀው።
ከማህበራዊ ቀውስ አንፃርም በስፖርት ውርርዱ የሚሳተፉ ሰዎች ሲሸነፉ የጤና ችግርን ጨምሮ የትዳር መፍረስ እና የቤተሰብ መበተንን እያስከተለ መሆኑም ተጠቅሷል።
ከዚህ ባለፈም ስንፍና፣ ሀብትን ለማፍራት የተሳሳተ መንገድ መከተል፣ የስራ ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆንን ጨምሮ ራስን እስከ ማጥፋት የሚደርሰ ስነ ልቦናዊ ቀውስ እያስከተለ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ወንዶች በውርርዱ ሲሸነፉ ቤት ገብተው የትዳር አጋራቸውን እስከ መምታት የሚደርስ ጥቃት ማድረስ እና ገንዘብ የሚከለክሉ ሲሆን ይህም ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በሴቶች ላይ እያደረሰ መሆኑም ተጠቅሷል።
ከዚህ አንጻርም ለጉዳዩ መፍትሄ ሊዘጋጅለት ይገባል ብሏል የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር።
የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ለስፖርት ውርርድ ተቋማት ፍቃድ መከልከል እና ፍቃድ ወስደው በሚሰሩት ላይም ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንዳለበት ተገልጿል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፥ የስፖርት ውርርዱ ካለው ተፅእኖ አንፃር ሙሉ በሙሉ መቆም አለበት የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሰሞኑን በተከታታይ በሰራቸው ዘገባዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ይህ የስፖርታዊ ውርርድ ጨዋታ በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን ተመልክቷል።
በዚሁ የውርርድ ጨዋታ ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶችም ሆነ የታዳጊዎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑንም ነው የታዘበው።
የውርርድ ተቋማት ተብለው ህጋዊ ፈቃድና እውቅና የተሰጣቸው ድርጅቶች፣ የዳበሩ ድረ ገፆች ያሏቸው፣ አማራጭ የአንድሮይድ መተግበሪያን የሚጠቀሙ እና አለፍ ሲልም ይህ ላልገባቸው በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የተለያዩ ቦታዎች የመወራረጃ ትኬትን መሸጣቸው ወጣቶች እና ታዳጊዎችን በቀላሉ እንዲይዙ እንዳስቻላቸው ይነገራል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዙሪያም እየተስፋፋ የመጣው ይህ የውርርድ ጨዋታ በተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ወደ ማሳደሩ ተሸጋግሯል።
የመወራረጃ አማራጮቹ አነስተኛ ከተባለው 10 ብር እስከ ተወራራጁ አቅም ድረስ የሚፈቅድ መሆኑም በርካቶችን በጨዋታው ሱስ በማስያዝ ለማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እየዳረጋቸው መሆኑን ከአስተያየት ሰጭ ወጣቶች ተረድተናል።
በኢትዮጵያ ያለው አሁናዊ መልክ አሳሳቢ መሆኑን ከወራት በፊት ያስነበበው ዓለም አቀፉ ተነባቢ መፅሄት ዘ ኢኮኖሚስት፥ “ኢትዮጵያ በቁማር በሽታ ተይዛለች” የሚል ርዕስን ሰጥቶ ለንባብ ባበቃው ዘገባ ከትንሹ 10 ብር እስከ መጠኑ ከፍ ባለ ገንዘብ የሚመደብበት የውርርድ ጨዋታ በማህበረሰቡ ዘንድ ስር የሰደደ ችግር ይዞ ስለመምጣቱ አንስቷል።
በሀገሪቱ 22 የሚሆኑ ድርጅቶች በስፖርታዊ ውርርድ ጨዋታ ላይ ፈቃድ አውጥተው እየሰሩ ይገኛሉ።
የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደርም በቅርቡ እየተስፋፋ ለመጣው ለዚህ የስፖርት ውርርድ ጨዋታ በጊዜያዊነት አዲስ ፈቃድ መስጠት ማቆሙን ማስታወቁ ይታወሳል።