የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሠራተኞች እውቅና ሰጠ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት 11 ወራት ከ39 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ባለፉት 11 ወራት ከ39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልፀው በዚህም የዕቅዱን 92 በመቶ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል ፡፡
የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለውም ቢሮው የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች በመስራቱና ሠራተኛው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣቱ ነው ብለዋል፡፡
ቢሮው በመዲናዋ በሚገኙ 16 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሠራተኞች እውቅና እና የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከ42 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ የአገር ልማትና እድገት የሚወሰነው በሚሰበሰበው ግብር በመሆኑ ግብር ከፋዮች በኃላፊነትና በታማኝነት መክፈል አለባቸው ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡