በነገው ዕለት በመስቀል አደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚደረግ እየተላላፈ ያለው መረጃ የተዛባ ነው-ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚደረግ እየተላላፈ ያለው መረጃ የተዛባ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ህገወጥ ስብሰባ ለማድረግ እንቅስቃሴ የሚደረግ ከሆነ በህግ አግባብ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን ለወጣቶችና ጎልማሶች ማህበራት ሕብረት በቁጥር ዘ1(1) 804 – መ1-13 -10 ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ በአዳራሽ ስብስባ እንዲደረግ እንደፈቀደ ነገር ግን በማይመለከታቸውና እና ውክልና ባልተሰጣቸው አካለት በስህተት በመስቀል አደባባይ ስብሰባው እንዲደረግ የተሰጠው ፈቃድ አግባብ አለመሆኑን ለኮሚሽኑ በግልባጭ ማሳወቁን ነው የገለፀው፡፡
ነገር ግን በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎችና በከተማው በተለጠፉ ማስታወቂያዎች ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው ህዝባዊ ስብሰባ በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ የሚገልፅ መረጃ እየተሰራጨ ቢሆንም ፤ የሰላም ሚኒስቴር ስብሰባውን በመስቀል አደባባይ ማድረግ የማይቻልበትን ዝርዝር ሁኔታ ለጥያቄ አቅራቢዎቹ በደብዳቤ ማሳወቁን ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ስለሆነም በተጠቀሰው እለት በመስቀል አደባባይ ይካሄዳል የተባለው ስብሰባው በከተማ አስተዳደሩም ይሁን በፖሊስ ኮሚሽኑ እውቅና የሌለው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመስቀል አደባባይ ስብሰባው ይደረጋል በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ የተዘባ መሆኑን ህብረተሰቡ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዲገነዘቡለት ኮሚሽኑ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
አየተሠራጨ ያለው የተዛባ መረጃ ህብረተሰብን ለማደናገጥ ፣ ለማሸበር እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት በህብረተሰቡ ላይ የፀጥታ ስጋት ለመፍጠር ሆን ተብሎ ታቅዶና ታስቦ እየተሰራጫ ያለ ሀሰተኛ መረጃ ነው ሲል ኮሚሽኑ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ሀሰተኛ መረጃ በስፋት የተሰራጨ በመሆኑ በሰዎች የእለት ከእለት እንቅስቃሴም ላይ አሉታዊ የስነ ልቦና ጫና እያሳደረ ነው፡፡
በመሆኑ የተዘባ መረጃ የሚያሰራጩ እንዲሁም መረጃን ተቀብለው የሚያናፍሱ ሆኑ ህገወጥ ስብሰባውን የጠሩ አካላት ከህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳስቦ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ላይ እና ህገወጥ ስብሰባ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ በሚገኙ አካላት ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎ ለሚያጋጥም ማንኛውም ችግር ኃላፊነቱን የሚወስደው ህገወጥ ስብሰባውን የጠራ አካል መሆኑን ነው ኮሚሽኑ የገለፀው፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!