ምርጫ ቦርድ ለአራት ፓርቲዎች የእውቅና ሰርተፍኬትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአራት የፖለቲካ ፓርቲዎች የእውቅና ሰርተፍኬትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።
ፓርቲዎቹም ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።
ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜያዊ የምዝገባ ሰርተፍኬት ማግኘት የሚቻለው ማመልከቻ፣ በጽሁፍ የምዝገባ ጥያቄ፣ ለሀገር አቀፍ ቢያንስ 200፣ ለክልላዊ ፓርቲ ቢያንስ 100 አመልካቾች የፈረሙበት የስብሰባ ቃለ ጉባኤ ማቅረብ ሲችሉ መሆኑ ተገልጿል።
እንዲሁም የሚመሰረተው የፓለቲካ ፓርቲ ጊዜያዊ ስም ማዘጋጀት ሲችል እና የምርጫ ህጉን እና ተያያዥ ህጎችን የሚያከብር ስለመሆኑ ማረጋገጫ እና ቦርዱ የሚወስነውን የአገልግሎት ክፍያ መፈፀም ሲችል መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህ ፍቃድ የሚያገለግለው ለሶስት ወራት ብቻ ሲሆን፥ አመልካቾች በቂ ምክንያት አቅርበው ከጠየቁ ለተጨማሪ 3 ወር ሊራዘም ይችላል ተብሏል።