የደብሊው ኤ የምግብ ዘይት ፋብሪካ በነገው ዕለት ይመረቃል
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ5. 2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የደብሊው ኤ የምግብ ዘይት ፋብሪካ በነገው ዕለት ይመረቃል።
የደብሊው ኤ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የፋብሪካው ባለቤት አቶ ወርቁ አይተነው፤ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ፋብሪካው ከሃገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ የሰሊጥ ዘይት ኤክስፖርት ያደርጋል ብለዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ፋብሪካው በቀን 1 ሚሊየን 350 ሺህ ሌትር ዘይት የማምረት አቅም አለው።
ፋብሪካው አሁን ላይ ለ አንድ ሺህ 500 ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ሲጀምር የምርት የሰራተኞቹ ቁጥር በ3 ፈረቃ እስከ 6 ሺህ ይደርሳል ተብሏል።
ጥሬ ሰሊጥ በመላክ በኩንታል ከሚገኘው ገቢ ይልቅ እሴት በመጨመር በዘይት መልክ መላኩ የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን በእጥፍ ያሳድገዋል ብለዋል አቶ ወርቁ።
በዚህም ከጠቅላላ ምርቱ 40 በመቶው የሰሊጥ ዘይት ይሆናል ተብሏል።
በዓመት እስከ 6 ሚሊየን ኩንታል የቅባት እህሎች የሚያስፈልጉት ፋብሪካው፣ ከወዲሁ አርሶ አደሮች የፋብሪካውን መገንባት ከግምት ያስገባ ስራ እንዲሰሩ ጥሪውን አቅርቧል።
በሌላ በኩል ለዘይቱ ስርጭት አከፋፋዮችን የማዘጋጀቱ ተግባር መከናወኑ የተገለጸ ሲሆን ፋብሪካው በገበያው ላይ ያለውን የዘይት እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል ተግባር ይከናወናልም ነው የተባለው።
በሃገር ውስጥ ገበያው ፍላጎት እና አቅርቦት መካከልም ያለውን ልዩነት በመድፈን የደብሊው ኤ የምግብ ዘይት ፋብሪካ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሀገር ውስጥ የዘይት ፍጆታውን 60 በመቶ ለመሸፈን ይሰራል ነው የተባለው።
የምርት መቆራረጥ እንዳይፈጠርም ፋብሪካው ምርቱን ወደ ገበያው በቅርቡ በተደራጀ መልኩ ያስገባል ነው በመግለጫው የተባለው።
በምስክር ስናፍቅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!