ያለፉት ሦስት ዓመታት የውሃ፣ የመስኖ እና የኢነርጂ ዘርፍ የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ላይ አተኩሯል – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለፉት ሦስት ዓመታት የውሃ፣ የመስኖ እና የኢነርጂ ዘርፍ የኢትዮጵያ ብልጽግና ራዕይ ዐበይት የስኬት ምዕራፎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን በማሟላት ዜጎች ክብራቸውን የጠበቀ ሕይወት እንዲኖሩ በማድረግ ላይ ማተኮራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሶስት አመታት በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በአጠቃላይ 56 ሺህ 790 የገጠርና የከተማ የውሃ ተቋማት ግንባታን በማጠናቀቅ 15 ሚሊየን 287 ሺህ 148 ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውል 16 ቢሊየን ብር የብድር ፋይናንስ ከተለያዩ አበዳሪ ተቋማት በማሰባሰብ ለ72 ከተሞች መጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውል የብድር ፋይናንስ ማቅረብ ተችሏልም ነው ያሉት።
በሃይል ዘርፍም ጊቤ 3፣ የገናሌ ዳዋ 3 የውሃ ማመንጫዎች እና የረጲ የደረቅ ቁሻሻ ማመንጫ ማጠናቀቅና ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
አሁኑ ወቅት ጠቅላላ የማመንጨት አቅም 4 ሺህ 466 ሜዋ እንዲሁም 19 ሺህ 746 ኪሎ ሜትር ጠቅላላ ርዝመት ያላቸው የማስተላለፊያ መስመሮች በሥራ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
ከ875 ሺህ በላይ ዜጎች የግሪድ አገልግሎት ሲያገኙ ከ1 ሺህ 100 በላይ የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም አስታውቀዋል።
ከመንግስት ወጪ ቅነሳ ጋር ተያይዞ ችግሮች የነበሩባቸውን ፕሮጀክቶች መፍትሔ በመስጠት 4 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የርብ፣ የጊዳቦ፣ የመቂ ዝዋይ እና የመገጭ ሰራባ የመስኖ ልማት ፕሮክቶችን ማጠናቀቅ 32 ሺህ 400 ሄክታር በማልማት 56 ሺህ 946 አርሶአደሮች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አውስተዋል።
እንቦጭን ከጣና ሀይቅ ማስወገድ ዘመቻ ከ4 ሺህ 302 ሄክታር ዉስጥ ከ3 ሺህ 56 ሄክታር በላይ ማስወገድ መቻሉንም አንስተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!