የጥምቀት በዓል በተለያዩ የአለም ሀገራትም ተከብሯል
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተለያዩ የአለም ሀገራት በሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ዓመታዊ በዓሎች አንዱ የጥምቀት በዓል ነው።
በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ያሉ የእምነቱ ተከታዮች የጥምቀት በዓልን በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ለዘመናት እያከበሩ እዚህ ደርሰዋል።
በዓሉ ከሚከበርባቸው ከእነዚህ ሀገራት መከካል 90 ሚሊየን የኦርቶዶክስ ተከታዮችን የያዘችው ሩሲያ ትጠቀሳለች።
የሩሲያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የእየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅን እና ሶስቱ ስላሴዎችን ለማስታወስ በበረዶ ውሃ ውስጥ ራሳቸውን ሶስት ጊዜ ይነከራሉ።
የሩሲያ ኦርቶዶክሳዊያን ለሶስት ጊዜያት ራሳቸውን በበረዶ ውሃ ውስጥ መንከር ሀጢያታቸውን ያነፃል ብለው ያምናሉ።
የእምነቱ ተከታዮች በጥምቀት ወቅት ሁሉም ውሃ የተቀደሰ መሆኑን የሚያምኑ ሲሆን፥ በረዶውም ጤናቸው ላይ በጎ ተፅዕኖ እንዳለውም ያምናሉ።
በተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም በጥልቁ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ በዋና ውድድር የታጀበን የጥምቀት በዓል ያሳልፋሉ።
በቦስኒያ እና ሄርዞጎቪኒያ የሚገኙት የእምነቱ ተከታዮች በቄሶች ወደ ውሃ የተጣለውን የእንጨት መስቀል ለመያዝ የሚደረግ የዋና ፉክክር ይደረጋል።
በዚህ የዋና ውድድር መስቀሉን መያዝ የቻለው እና ወደ መሬት የመለሰው ግለሰብ ዓመቱን በሙሉ የተባረከ ይሆናል ብለውም ያምናሉ።
በተመሳሳይ የጥምቀት ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ባለው ስርዓት በኤርትራ ተከብሮ ውሏል፡፡