Fana: At a Speed of Life!

የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠና ጥራት ማረጋገጫ ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠና ጥራት ማረጋገጫ ማዕከል በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው።

የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ በቴክሎጂ የታገዘ የተግባር ትምህርት እንዲስፋፋ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል።

የግንባታውን የመሰረት ድንጋይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንትባ አዳነች አቤቤ አስቀምጠዋል።

ማዕከሉ በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በ2 ሄክታር መሬት ላይ ይገነባል ተብሏል።

ግንባታው ከዓለም ባንክ በተገኘ የ10 ሚሊዮን ዶላር የሚካሄድ ሲሆን በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ የትምህርት ጥራት በማስጠበቅ ረገድ ክፈተቶች አሉ ብለዋል።

ይህንንም ክፍተት ለመሙላትና በዘርፉ እየተንከባለለ ያለውን የጥራት ጥያቄ ለመመለስ ማዕከሉ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።

ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ጀምሮ እስከ ተለያዩ የትምርት ማረጋገጫ ሥራዎች እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በቴክሎጂ የታገዘ የተግባር ትምህርት እንዲስፋፋም ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ጎን ለጎንም በአገሪቱ የሚሰጡ የከፍተኛና የቴክኒክ ሙያና ሥልጠና ፕሮግራሞች በአንድ ቋት እንዲመሩና ጥራት ባለው መልኩ እንዲከወን ያስችላል ብለዋል።

ይህም በአገሪቱ በዘርፉ ያለውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በማዘመን ረገድ አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ማዕከሉ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑና ከዘመኑ ጋር ተወዳዳሪ የሰው ሃይል እንዲፈራ በማድረግም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንትባ አዳነች አቤቤ፤ ማዕከሉ ክፍተት የሚታይበትን የትምህርት ጥራት በማስተካከል ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ማዕከሉ በከተማዋም ሆኖ በአገሪቱ ለሚካሄዱ የተለያዩ ልማቶች ብቁ የሆኑ የሰውሃይልና ተቋም ለማፍራት የሚደረገውን ጥረትም ይደግፋል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በከተማ ለመገንባት የሚያስበውን የትምህርት ቱሪዝም በመደገፍ ማዕከሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

 

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.