ሰባት የመንግስት የልማት ድርጅቶች 780 ቢሊየን ብር የሀገር ውስጥና የውጭ እዳ እንዳለባቸው ተረጋገጠ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰባት የመንግስት የልማት ድርጅቶች 780 ቢሊየን ብር ወይም 19 ቢሊየን ዶላር የሀገር ውስጥና የውጭ እዳ እንዳለባቸው ማረጋገጡን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ለማክሮ ኢኮኖሚው አለመረጋጋት ምላሽ ለመስጠት መንግስት ከልማት ድርጅቶች ብድር እና መሰረታዊ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለፀው።
በዚህም መንግስት ሁሉን አቀፍ ግምገማ ካካሄደ በኋላ ሰባት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከፍተኛ የብድር እዳ እንዳለባቸው ተለይተዋል ብሏል።
ድርጅቶቹም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ፣የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ፣ ኢትዮ ኢንጅነሪግ ግሩፕ(የድሮው ሜቴክ)፣ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና ስኳር ኮርፖሬሽን ናቸው።
እነዚህ ድርጅቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በሀገር ወስጥ 780 ቢሊየን ብር እዳ ተገኝቶባቸዋል።
ባለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ በሰው ሃብት ልማት ወሳኝ መሻሻል ብታሳይም ከህዝብ መር ኢንቨስትመነት እና ብድርን መሰረት ካደረገው የመሰረተ ልማት ሞዴል ጋር በተያያዘ የፋይንስ አለመረጋጋት እንደተፈጠረ ተነግሯል።
ነገር ግን እነዚህ ኢንቨስትመንቶች የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለሟሟላት ወሳኝ እንደነበሩ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የፋይናንስ ሞዴሉ የራሱ ችግሮች እንደነበሩት ያስታወቀው ሚኒስትሩ ባለፉት 10 ዓመታት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ብድር 21 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አስታውቋል።
መንግስት ለዚህ ችግር መፍትሄ ለመስጠት የእርምት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ እና ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ኢንቨስትመንትና ፋይናንስ ቀጣይነት ያለው አዲስ ሞዴል እያዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን