Fana: At a Speed of Life!

የሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበር በአዲስ አበባ ደረጃ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ዓለም አቀፉን የሸማቾች መብቶች ጥበቃ ቀን ዛሬ ሲያከብር፤ በአዲስ አበባ ደረጃ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበርም በይፋ ተመስርቷል።

የማኅበሩ መመስረት በነጋዴውና በሸማቹ መካከል መልካም ግንኙነት በመፍጠር ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስችል ተገልጿል።

ማኅበሩ ሸማቹ ከነጋዴው ገዝቶ በተጠቀመው ምርት ሳቢያ ጉዳት ቢደርስበት እንኳ ካሣ እንዲያገኝ የሚያደርግ ስልጣን እንደሚኖረው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የገበያ አሻጥር እየተስተዋለ፤ ሸማቹም የችግሩ ገፈት ቀማሽ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት አቶ ዣንጥራር የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ምርቶች በሸማቾች ማኅበራት በኩል እየቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዲያም ሆኖ ችግሩን ለመፍታት ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ የማኅበሩ መመስረት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር አክለዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ በበኩላቸው፤ መንግስት የሸማቹን ማኅበረሰብ ፍላጎት ለማርካት የንግድ ስርዓቱን ዘመናዊና ፍትሃዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የማኅበሩ መመስረት ሸማቾች በሕገ ወጥ ነጋዴዎች እንዳይጎዱ በመታገል ረገድ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ሸማቾች ስለሚገዙት ምርት ትክክለኛ መረጃ አግኝተው ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ግዥ እንዲፈጸሙም ያግዛል ነው ያሉት።

የንግድ ሕግና አሰራርን በመጣስ ሸማቾችን የሚበድሉ ነገዴዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ሃላፊው እነዚህን ሕገወጥ አካላት በተደራጀ መልኩ ለሕግ ለማቅረብ የሚያግዝ አደረጃጀት እንደሆነም አክለዋል።

ማኅበሩ ሚዛን የሚሸቅቡና ጥራት የጎደለው ምርት የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ምንም አይነት ግዥ እንዳያገኙ በማድረግ ከገበያ እንዲወጡ እስከማድረግ የሚደርስ ውሳኔ ያሳልፋል።

በሌላ በኩል ለሸማቾች ተገቢውን ምርት በፍትሃዊነት የሚያቀርቡ ነጋዴዎችን የሚያበረታታ ሁኔታ ይፈጠራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሸማቾች መብቶች ጥበቃ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ፤ በኢትዮጵያ ለ8ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.