ባልደራስ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል የፓርቲ ቅድመ-ምስረታ ጉባኤ እንዳላካሂድ ተከልክያለሁ በሚል ላነሳው ቅሬታ ሆቴሉ ምላሽ ሰጠ
አበባ፣ ጥር 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባልደራስ በሆቴሉ አዳራሽ ሊያካሂደው የነበረውን ስብሰባ የተከለከለው ቀደም ሲል ከተያዘ ፕሮግራም ጋር የድምጽ መረባበሻ እንዳይኖር በሚል ሃሳብ ምክንያት መሆኑን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) በፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ 11/62 ለምርጫ ቦርድ ቅድመ ምስረታ ለማካሄድ ዛሬ በኢንተር ኮንቲነንታል ሆቴል የጠራውን ጉባኤ እንዳያካሂድ መከልከሉን አስታውቆ ነበር።
የሆቴሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወገኔ ማቲዎስ ከባልደራስ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክተው ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በትናንትናው ዕለት ስንታየሁ ቸኮል የተባሉ ግለሰብ ለ200 ሰዎች መሰብሰቢያ የሚሆን አደራሽ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ፈጽመው መሄዳቸውን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በተከራየው አዳራሽ የተለያዩ የድምጽ መሳሪያዎችን በመጠቀም የሚያከናውነው የምርቃት ስነ ስርዓት መኖሩን ዘግይተው መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም ፕሮግራሙ በአንድ አዳራሽ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ክፍሎች የሚካሄድ በመሆኑ መረባበሽ እንዳይኖር አቶ ስንታየሁ ቸኮል የተባሉትን ግለሰብ ስብሰባቸውን እንዲያራዝሙት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ስልክ ደውለው ማሳወቃቸውን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ በወቅቱ በሃሳቡ ዙሪያ መግባባት ላይ ሳይደርሱ መቅረታቸውን ነው አቶ ወገኔ ያስረዱት።
ጉዳዩ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለም አቶ ስንታየሁ የተባለው ግለሰብ ዛሬ ጠዋት ስብሰባውን ለማካሄድ ከተሰብሳቢዎች ጋር ወደ ሆቴሉ መምጠታቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ወቅትም ስብሰባውን የሚያካሂደው የባለደራ ምክር ቤት አባላት መሆናቸውን መረዳታቸው የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ ፥ኪራዩን የፈጸመው ግለሰብ ስብሰባው የባለደራ ምክር ቤት መሆኑን እንዳላሳወቃቸው ተናግረዋል።
በዚህ ወቅትም ትናንት ባሳወቁት መሰረት በስብሰባው መረባበሽ እንዳይፈጠር ስብሰባውን ለሌላ ቀን እንዲያራዝሙ እና በሌላ በፈለጉት ቀን ማካሄድ እንደሚችሉ በድጋሜ መጠየቃቸውን ተናግረዋል ።
ይሁን እንጂ በሃሳቡ ዙሪያ አለመግባባት ተፈጥሮ ወደ ሆቴሉ እንገባለን ሲሉ በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በማሳወቅ ችግሩ እልባት ማገኘቱን ተናግረዋል።
ሆቴሉ ባልደራስ ስብሰባውን እንዲያራዝም የጠየቀውም ቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ከእነሱ ቀድሞ አዳራሹን የተከራየ በመሆኑ እንጂ በማንም ጣልቃ ገብነትአለመሆኑን ገልፀዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) አመራሮች ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ ስልክ ባለማንሳታቸው አልተሳከም።