የአየር ንብረት ብክለት በአዕምሮ ጤና ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ጥናት አመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተመራማሪዎች የአየር ንብረት ብክለት በአዕምሮ ጤና ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስታወቁ።
ለበርካታ አመታት በሰዎችና በእንስሳት ላይ ባደረጉት ጥናት የአየር ንብረት ብክለት በሰው አካል እና በአዕምሮ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አስታውቀዋል።
እንደተመራማሪዎቹ ገለጻ ለረጅም ጊዜ የአየር ንብረት ብክለት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በአዕምሯቸው ውስጥ እብጠት ይፈጠራል።
ይህ ደግሞ ለጭንቀት፣ የሰውነት መድከም፣ ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት፣ ለእንቅልፍ እጦት፣ ለነርቭና ተያያዥ ችግሮች ይዳርጋል ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም ከፍተኛ ጭንቀት እንዲሁም የስሜት መቀያየር እና ድብርት በአየር ንብረት ብክለት ምክንያት እንደሚከሰቱም ጠቅሰዋል።
መሰል ተደራራቢ ችግሮች ደግሞ ለአእምሮ ጤንነት ችግር ይዳርጋሉም ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ።
በተጨማሪም የመተንፈሻ አካላት፣ የልብና የደም ቧንቧ ላይ ችግር እንደሚያስከትልም ነው የገለጹት።
ተመራማሪዎቹ ከልጅነት ጀምሮ ለአየር ንብረት ብክለት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በዚህ ችግር የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ይሁን እንጅ የአየር ንብረት ብክለት ተጋላጭ መሆን ከሰዎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤንነት ሁኔታ ጋር ስላለው ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት በቀጣይ ተጨማሪ ጥናቶችን ይደረጋሉ
ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአየር ንብረት ብክለት በየዓመቱ ወደ 3 ሚሊየን ሰዎች ህልፈት ምክንያት መሆኑን ይገልጻል።
ምንጭ፦ psychologytoday.com