Fana: At a Speed of Life!

አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ማሪያና ዓይኒ ዋሪ በዓል በዩኔስኮ አንዲመዘገብ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ማሪያና ዓይኒ ዋሪ በዓል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት መጠናቀቁን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
የባለስልጣኑ የባህል ተመራማሪ አቶ ገዛኸኝ ግርማ የአሸንዳ፣ ሻደይና አሸንድዬ የልጃገረዶች በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ሰዓትም በዓሉ በማይዳሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ የማስመረጫ ሰነድና አስፈላጊ ጥናቶች ዝግጅት ተጠናቆ በመጭው መጋቢት ወር እንደሚላክ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዓሉ በመንግስታቱ ድርጅት በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚወሰን ከሆነ የኢትዮጵያ አምስተኛው የማይዳሰስ የዓለም የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ይሆናል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እንደገና ደሳለኝ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህል ሃብትና አቅም አንጻር በቱሪዝሙ የሚፈለገውን ያህል አለመጠቀሟን ተናግረዋል።
ሃላፊው በአሁኑ ወቅት 8 የሚሆኑ ታላላቅ ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች በዩኔስኮ ጊዜያዊ መዝገብ ላይ ሰፍረው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በዩኔስኮ መመዝገብ ሀገሪቷ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ከማሳደጉ ባሻገር የአማራና የትግራይ ክልሎችን ህዝቦች ይበልጥ የሚያቀራርብና የሚያስተሳስር እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት ያስመዘገበቻቸው በዓላት የመስቀል ደመራ፣ የጥምቀት፣ ፍቼ ጨምበላላ እና የገዳ ስርዓት መሆናቸው ይታወቃል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.