በአዲስ አበባ ከተማ ከ5 እስከ 8ኛ ክፍል የገጽ ለገጽ ትምህርት ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የ2013 የትምህርት ዘመን ከ5 እስከ 8ኛ ክፍል የገጽ ለገጽ ትምህርት በዛሬው ዕለት ተጀመረ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መካኒሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ትምህርት አስጀምረዋል ።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ልዩ ጥንቃቄ ለማድረግ ከ2 ሺህ 300 በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እና 118 የመመገቢያ አዳራሾች መገንባቱን ገልጸዋል ።
አጠቃላይ የመማር ማስተማሩ ሂደት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በጸዳ መንገድ እንዲካሄድ ተማሪዎች መምህራን እና ወላጆች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች በትምህርት ማስጀመር መርሐግብር ላይ ለተማሪዎች የተዘጋጀ ዩኒፎርም፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ለመምህራን ደግሞ የጋውን ስጦታ አበርክተዋል።
እንዲሁም በሌሎች የመዲናዋ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ትምህርት መጀመሩን በማስመልከት የገጽ ለገጽ የመማር ማስተማሩ ተግባር የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡
መርሃ ግብሩ በወይዘሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በህዝብ ንቅናቄ እየተከናወነ መሆኑን ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡