የድሬደዋና ባህርዳር ከተሞችን የመንግስት አገልግሎት በአንድ መስኮት ለመስጠት የሚያስችል የ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 24 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የድሬደዋና ባህርዳር ከተሞችን የመንግስት አገልግሎት በአንድ መስኮት ለመስጠት የሚያስችል የ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት በአውሮፓ ኮሚሽንና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መካከል ተፈርሟል።
የድጋፍ ሥምምነቱ የሀገሪቱን የስራ ቅልጥፍና ለማሳለጥ የተነደፈ ፕሮግራም የሚያግዝ የዲጂታል ሪፎርም ፕሮጀክት ትግበራን የያዘ ነው ፡፡
በስምምነቱ መሠረት የአውሮፓ ኮሚሽን ለፕሮጀክቱ ትግበራ የ1ነጥብ 2 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዮት ባዩ እና በአውሮፓ ኮሚሽን የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ቡድን መሪ ሳኒ ዊልየምስ ፈርመውታል።
በዚሁ ወቅት ዶክተር አብዮት ባዩ ድጋፉ ሚኒስቴሩ ለሥራ ቅልጥፍና በተነደፈው ፕሮግራም ሥር ያለውን የዲጂታል ሪፎርሙን ለመምራትና ለመተግበር ያግዘዋል ብለዋል።
በዚህ መርሃ ግብር የባህርዳርና ድሬደዋ ከተሞች የብሔራዊ የንግድ ፖርታል አካል እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
በአውሮፓ ኮሚሽን የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ቡድን መሪ ሳኒ ዊልየምስ በበኩላቸው÷ ድጋፉ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታይዜሽን ስራን በማገዝ በንግዱ ዘርፍና በኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የመንግስት ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን ዜጎች ባሉበት ሆነው ማግኘት እንዲችሉ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሥርዓት (ትራንዛክሽናል ፖርታል) እንዲኖራቸው ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በ2019 በሥራ ቅልጥፍና ከ 190 ሀገራት 159ኛ ደረጃ ላይ የነበረች ሲሆን ÷ይህ ፕሮግራም በ2021 ይህንን ደረጃ በማሻሻል ከመጀመሪያዎቹ 100 ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ለያዘችው ዕቅድ ስኬት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው መገለጹን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!