ዓመታዊ የፅዮን ማርያም ንግስ በዓልን ህዝቡ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲያከብር የፀረ-ሽብር ልዩ ኮማንዶ ስኬታማ ስራ አከናውኗል – የፌደራል ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል መከላከያ ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የህብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት እንዲከበርና ህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮውን እንዲመራ ህግ የማስከበር ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከሀዲው የህወሓት ቡድን የሀገር ሉዓላዊነትን በመዳፈር በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ በፈፀመው ጥቃት የተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ በድል እንደ ተጠናቀቀ አስታውሷል።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በህግ የሚፈለጉ ተጠርጣሪ የጁንታው ህወሓት ቡድን አባላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የፀረ-ሽብር ልዩ ኮማንዶ ሀይል ወደ አካባቢው በማሰማራት የክትትል ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጿል።
ለአብነትም ወደ አክሱም ከተማ የገባው የፀረ-ሽብር ልዩ ኮማንዶ ሀይል ህዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም በአክሱም ከተማ የተከበረውን ዓመታዊ የፅዮን ማርያም ንግስ በዓልን ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲያከብር ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በአካባቢው ፀጥታ የማስከበር ስራ መስራቱን ኮሚሽኑ ጠቁሟል
በዚህ ወቅት ከሀዲው የጁንታው ህወሓት ቡድን ለእኩይ ተግባር ሊጠቀምበት የነበረ የተለያዩ የጦር መሳሪዎች መያዝ ተችሏልም ነው ያለው ኮሚሽኑ።
ይህ መስዋዕትነት ተከፍሎበት እየተሰራ ያለው ህግን የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!