የባህር ዳር ፈለገ ህይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በባህር ዳር የሚገኘው የፈለገ ህይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመሰረተ ልማት እና በህክምና ግብአቶች እጥረት ምክንያት በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ ገለፀ።
ሆስፒታሉ ከተመላላሽ ህክምና ጀምሮ የካንሰር ህክምና፣ኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንዲሁም የቀዶ ሕክምናን ጨምሮ ከ16 በላይ የተለያዩ የህክምና አገልግሎት ይሰጡበታል፡፡
አሁን ግን ሆስፒታሉ ባጋጠሙት የክፍል ጥበት፣ የአልጋ ውስንነት፣ በተለይም የህክምና ግብአት እጥረት ችግሮች የሚፈለገውን ያክል አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን የሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል ሀላፊ ዶክተር አዲሱ መለሰ ለፋና ተናግረዋል።
እንዲሁም የበጀት እጥረት እና ሆስፒታሉ ያለበት የ30 ሚሊየን እዳ በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ምክንያቶቹ እና ያስከተሉትም ችግሮች ታካሚዎቹ የህክምና አገልግሎትን ማግኘት እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ነው የተናገሩት።
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ አብይ ፍስሀ በበኩላቸው ሆስፒታሉ 600 አልጋዎች ቢኖሩትም ከታካሚው ጋር ሊመጣጠን አለመቻሉ ተጨማሪ ችግር ሆኗል ነው ያሉት።
ስለችግሮቹ የተጠየቀዉ የክልሉ ጤና ቢሮ የሆስፒታሉን የመሰረተ ልማት ችግር የሚፈታ ከ600 በላይ አልጋዎች ያለው ማስፋፊያ እየሰራ እንደሆነ አስታውቋል።
የግብአት እጥረቶቹን እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አሰራርም እንደተዘረጋ በመግለጽ።
ከተመሰረተ ከ50 አመት በላይ ያስቆጠረው በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔላይዝድ ሆስፒታል በዓመት ከ 5 እስከ 7 ሚሊየን ለሚደርሱ ህሙማን የህክምና አገልግሎት ይሰጣል።
በዙፋን ካሳሁን