የመከላከያ ሰራዊት መቐለ ከተማን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል- ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመከላከያ ሰራዊት መቐለ ከተማን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ አስታወቁ።
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ነው የመከላከያ ሰራዊት መቐለ ከተማን መቆጣጠሩን ያስታወቁት።
ጀኔራል ብርሀኑ ጁላ በመግለጫቸውም፥ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በትናንትናው እለት የመቐለ ከተማ ነዋሪ ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዴት ከተማዋን መቆጣጠር ይቻላል በሚለው ላይ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ይህንን ተከትሎም በዛሬው እለት ከሰዓት ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል ብለዋል በመግለጫቸው።
በአሁኑ ወቅትም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በየጎሬው የተደበቁ የጁንታው የህወሓት አባላትን እያሳደደ እና እያደነ ይገኛል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀደም ብለው በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃ “በዚህ ዘመቻችን ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት ተችሏል” ብለዋል።